
ደብረታቦር: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንደነበረች እና ላለፉት 30 ዓመታት ባልተገባ መንገድ ከባሕር በር ባለቤትነት ውጭ ኾና እንደቆየች ታሪክ ያስረዳል።
የባሕር በር የሕልውና ጉዳይ በመኾኑ የሀገሪቱን የባሕር በር ባለቤትነቷን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ እየሠራች ትገኛለች።
አሚኮ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የደብረታቦር ከተማ ነዋሪ አቶ እንዳልካቸው ዳምጠው ኢትዮጵያ በዓመት ለቀረጥ የምታወጣው ወጭ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል።
ለዚህም የባሕር በር ባለቤትነቷ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
የባሕር በር የማግኘት ጥያቄን እውን በማድረግ በሕዳሴው ግድብ የታየውን አንድነት መድገም እንደሚገባም አብራርተዋል። ወደ ልማትም መሸጋገር ይገባል ነው ያሉት።
ሌላኛዋ ሃሳባቸውን ያጋሩን የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ፍቅር ሳህሉ የባሕር በር ጥያቄ የቆዬ የሕዝብ ጥያቄ እንደኾነ እና መመለስ ያለበት እንደኾነም አስረድተዋል።
የቀይ ባሕር እና የኢትዮጵያ ትስስር ረጅም ታሪክ ያለው ነው ያሉት ወይዘሮ ፍቅር ስለ ሀገሪቱ የቀይ ባሕር ባለቤትነት ታሪክ ምስክር ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የነበራትን የባለቤትነት ሁኔታ አሁን ላይ እውን ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኀላፊነት እንደኾነም ተናግረዋል።
መምህር ገረመው ታደሰም “መልክ ሠርቶ ያለአፍንጫ፤ ቤት ሠርቶ ያለ መውጫ” አይቻልም እንደተባለ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ተገቢ እንደኾነ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያም የባሕር በር ሳይኖራት መቀጠል የማይታሰብ ነገር መኾኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የባሕር በር አስፈላጊነትን ጠንቅቆ ማወቅ ይገባልም ብለዋል።
ሁሉም ዜጋ የጥያቄውን አግባብነት መረዳት እንደሚገባውም ጠቁመዋል። መምህሩ ለዚህ ተግባር መንግሥት ያሳየውን ቁርጠኝነት መደገፍ ይገባል ነው ያሉት።
መምህር ገረመው ኢትዮጵያ የባሕር በር የሚያስፈልጋት ለቅንጦት ሳይኾን የሀገሪቱን ከፍታ ለማረጋገጥ ወሳኝ በመኾኑ እንደኾነ አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
