ኢንዱስትሪዎች የአካባቢን ጥሬ ዕቃ በመጠቀም ተኪ ምርቶችን እያመረቱ ነው።

5
ደብረብርሃን: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአካባቢን ጥሬ ዕቃ በመጠቀም ወደ ሥራ የገቡ ኢንዱስትሪዎች 8 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶች ማምረታቸውን የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታውቋል።
ወደ ሥራ ከገቡ እና ተኪ ምርቶችን እያመረቱ ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች መካከል የአር ዜድ ኤክስ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ይገኝበታል።
የአር ዜድ ኤክስ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የንብረት ክፍል ኀላፊ አብርሃም ከተማ ፋብሪካው በርካታ የሀገር ውስጥ ጥሬ እቃዎችን በመጠቀም ኮምፎርት፣ አንሶላ እና የትራስ ልብሶችን እያመረተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ፋብሪካው ያመረታቸውን ምርቶችም ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ነው ብለዋል።
ንብረትነቱ የአማራ ደን ኢንተር ፕራይዝ የኾነ ጥሬ ዕቃን በመጠቀም የሀገር ውስጥ ገበያን ለማርካት እየተሠራ መኾኑን የገለጹት ደግሞ የደብረ ብርሃን እንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ኀላፊ ጌታቸው ይልማ ናቸው።
ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማምረት ከግለሰብ እስከ ድርጅት ድረስ ቋሚ ደንበኞች እንዳሉ ያነሱት አቶ ጌታቸው ምርቱንም ለአካባቢው ነዋሪዎች እያቀረበ እንደኾነ አንስተዋል።
በደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የአካባቢን ጥሬ እቃ በመጠቀም ስምንት ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርት እያመረቱ እንደሚገኙ የከተማ አሥተዳደሩ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ብርሃን ገብረሕይወት ተናግረዋል።
የአካባቢን ጥሬ ዕቃ በመጠቀም ወደ ሥራ የገቡ ኢንዱስትሪዎች 8 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶች ማምረታቸውን ነው ያብራሩት።
ወደ ሥራ ከገቡት ኢንዱስትሪዎች መካከል 4 ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻላቸውን ጠቁመዋል።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለማስቀረት በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ 74 የአካባቢ ጸጋዎችን በመለየት በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።
የሚመረቱ ምርቶች ለአካባቢው ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ በጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች፣ በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል እንዲቀርብ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር በ2018 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 46 ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መኾኑንም አመልክተዋል።
ዘጋቢ፦ ስንታየሁ ኃይሉ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየተሰጣቸውን ኀላፊነት በመወጣት ለሀገር ሰላም እና ልማት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የመንግሥት ሠራተኞች ገለጹ።
Next article“ማንም ፈለገም አልፈለግም ኢትዮጵያ ተዘግታ አትኖርም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)