የተሰጣቸውን ኀላፊነት በመወጣት ለሀገር ሰላም እና ልማት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የመንግሥት ሠራተኞች ገለጹ።

9
ጎንደር: ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር “የውጭ ባዳዎችን እና የውስጥ ባንዳዎችን ቅዥት በማምከን አንጸባራቂ ድሎችን እናስመዘግባለን” በሚል መነሻ መልእክት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ በከተማው የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ተሳታፊ ኾነዋል። ውይይቱ በስድስት ማዕከላት እየተካሄደ ሲኾን አሚኮ በተገኘበት የፋሲል ክፍለ ከተማ እና የጃንተከል ክፍለ ከተማ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሰላምን ለማስፈን በጋራ መሥራት እንደሚገባ አንስተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የጸጥታ ችግር ዜጎችን ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ተጽዕኖዎች መዳረጉን አንስተዋል።
ከዚህ ችግር ለመውጣት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል። መንግሥት በቀጣይም ሰላምን ለመገንባት ውይይትን በማስቀደም በትኩረት እንዲሠራም ነው ያሳሰቡት።
የመንግሥት ሠራተኞች ከመንግሥት እና ከሕዝብ የተሰጣቸውን ኀላፊነት በመወጣት ለሀገር ሰላም እና ልማት የበኩላቸውን እንደሚወጡም አሳውቀዋል።
የፋሲል ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አለባቸው ጀምበር ኢትዮጵያ ከውጭም ኾነ ከውስጥ ፈታኝ ሁኔታዎች የገጠሟት ቢኾንም ይህንን ተቋቁማ የልማት ሥራዎችን እየከወነች መኾኗን አንስተዋል። ለዚህም ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ለሀገር ግምባታ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ኀላፊነት እንዳለበትም አስረድተዋል። ሰላም የሚጀምረው ከራስ በመኾኑ የሰላም ባለቤት መኾን አስፈላጊ እንደኾነም ገልጸዋል።
መንግሥት የሰላም፣ የኢኮኖሚ፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግምባታ፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት እና ሌሎችንም የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን እየከወነ መኾኑን አረጋግጠዋል።
የመንግሥት ሠራተኞችም ኀላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
የጃንተከል ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ግርማቸው አስማማው መንግሥት ሠራተኞች እንደ አንድ የኅብረተሰብ ክፍል ለሰላም ያላቸውን አበርክቶ ገልጸዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት በመወጣት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመፍታት ለሰላም የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ሀገራዊ ምርጫው ወቅቱን ጠብቆ ይካሄዳል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleኢንዱስትሪዎች የአካባቢን ጥሬ ዕቃ በመጠቀም ተኪ ምርቶችን እያመረቱ ነው።