
ባሕር ዳር: ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የክልሉ የፖሊስ አባላት የእውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው የሥራ መመሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉ መንግሥት ለሰላም ግንባታ እና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ለሰላም መረጋገጥ የተደራጀ የሕዝብ ሃብት፣ ብቃት እና ቁርጠኝነት ያለው የጸጥታ ኃይል ይጠይቃል ነው ያሉት። ለዚህም የተሟላ ግንዛቤ እና የጠራ አመለካከት ያለው የፖሊስ ኃይል መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ የክልሉን ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት በመጠበቅ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ተልዕኮ ተሰጥቶት የተቋቋመ መኾኑን አንስተዋል።
በዚህ ተልዕኮው ውስጥ የፖሊስ አባላት መስዋዕትነት ከፍለው የክልሉን ሕዝብ ደኅንነት በመጠበቅ ሁነኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
ሽልማት እና እውቅና በፖሊስ ሠራዊት አንዱ የግንባታ አካል መኾኑን የገለጹት ርእሰ መሥተዳድሩ የተሠጠው እውቅናም ቀጣይነት ያለው የአመራር ብቃት በማሻሻል ለቀጣይ ተልዕኮ የሚያዘጋጅ መኾኑን አመላክተዋል።
በየደረጃው የሚገኘውን የፖሊስ ሠራዊት አባል ለማነቃቃት እና ለማትጋትም ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
ለዚህ ትልቅ የሙያ ዘርፍ ስምሪት እና ግዳጅ ወስደው ሕዝብን ለሚያገለግሉ የሠራዊቱ መሪዎች እና አባላት እውቅና መሥጠት ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
በየደረጃው ላላችሁ የፖሊስ አባላት የተሰጣቸው እውቅናም ለከፈሉት የሕይዎት መስዋዕትነት እና ተጋድሎ የተሠጠ ከፍ ያለ ትርጉም ያለው እንደኾነ ነው የገለጹት።
ፖሊስነት ዓለም አቀፍዊነት እሳቤ ያለው ሙያ መኾኑን ያመላከቱት ርእሰ መሥተዳድሩ “የፖሊስ ሠራዊቱ ዘረኝነትን፣ አድሏዊነትን፣ ሌብነትን እና ጎጠኝነትን የሚጸየፍ መኾን አለበት” ነው ያሉት።
የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለመዳፈር የሚፈልጉ ኃይሎችን እና የውስጥ ሰላማችንን ለመንሳት የሚፈልጉ ሕገ ወጦችን አደብ ለማስገዛት ብቁ የኾነ ኃይል እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።
ዘመኑ በፈጠረው ቴክኖሎጅ የሚፈጸሙ ውስብስብ ወንጀሎችን መከላከል የሚችል ብቁ ወታደር ኾኖ መገኘት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የፖሊስ ተቋም ሁሌም መማር፣ ራስን ማስተካከል እና ተልዕኮ ለመፈጸም ዝግጁ መኾንን ይጠይቃል ብለዋል።
የሕዝባችንን ሰላም እና ደኅንነት እንዲጠበቅ፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ ለላቀ ተልዕኮ ለመዘጋጀት የፖሊስ ተቋሙ ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ለተልዕኮ የሚያስፈልግ የሠራዊት ግብዓት ለማሟላት የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ መኾኑንም አረጋግጠዋል።
ዛሬ የተሰጠው እውቅና እና ሽልማት ለቀጣይ ተልዕኮ አደራ የጣለባችሁ መኾኑን አውቃችሁ ለቀጣይ የላቀ ግዳጅ እንድትዘጋጁ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
