ትምህርት ለትውልድ ግንባታ ያለውን ፋይዳ በመረዳት በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል።

2

ፍኖተሰላም: ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ የአንደኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና ወደ ትምህርት ገበታ ያልመጡ ተማሪዎች የምዝገባ ንቅናቄ መድረክ ከዞን፣ ከሁሉም ወረዳዎች እና ከከተማ አሥተዳደር መሪዎች፣ ባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በፍኖተሰላም ከተማ አካሂዷል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ተወካይ አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ሙሉጌታ ዓለም ትምህርት የአንድ ሀገር የተማረ የሰው ኀይል ማውጫ መሳሪያ መኾኑን ገልጸዋል።

በጸጥታ ችግሩ የትምህርት ዘርፉ ክፉኛ መጎዳቱን እና በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን አንስተዋል።

የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ሥራ ለማስጀመር ባለድርሻ አካላት ሚናቸው የጎላ በመኾኑ በርብርብ መሥራት ይገባል ነው ያሉት። በተለይ ትምህርት ለትውልድ ግንባታ ያለውን ፋይዳ በመረዳት አጀንዳ በማድረግ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ የስጋት ደሴ በ2018 የትምህርት ዘመን በምዕራብ ጎጃም ዞን 426 ሺህ 29 ተማሪዎች መማር ቢኖርባቸውም እስካሁን ወደ ትምህርት ቤት የመጡ ተማሪዎች ግን በሚጠበቀው ልክ አይደለም ነው ያሉት።

በቀጣይ ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎችን የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል። በዞኑ ካሉ 600 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 491 ትምህርት ቤቶች በጸጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው መኾኑንም ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ 161 ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን ጠቁመዋል።

ተማሪዎችን ከመመዝገብ በተጨማሪ ኅብረተሰቡን፣ አጋር እና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የማቋቋም ተግባራት እየተከናወኑ መኾናቸውንም አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት በወረዳው ትምህርት የጀመሩ ትምህርት ቤቶች እንዲቀጥሉ ኅብረተሰቡ በባለቤትነት መሥራቱን የሰከላ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይሄነው አማረ ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ በዚህ ዓመትም ትምህርት ቤቶችን የመጠበቅ እና የመንከባከብ ተግባር እያከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ትምህርት ከማስጀመር ጎን ለጎን ኅብረተሰቡን እና አጋር አካላትን በማስተባበር የትምህርት ተቋማትን ገጽታ የማሻሻል ሥራ እየሠሩ መኮናቸውን የደምበጫ ዙሪያ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አላዛር ተጎዴ አስገንዝበዋል።

በዚህም ከ50 ሚሊዮን በላይ ብር ወጭ ከ18 በላይ ትምህርት ቤቶች ጥገና እና መልሶ የማቋቋም ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ኅብረተሰቡን በማሳተፍ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ትምህርት ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እውቅና እና ሽልማቱ ለሁሉም የፖሊስ ሠራዊት የማንቂያ ደወል ነው” ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር)
Next article“የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የቀጣናውን የኢኮኖሚ ውህደትና የጋራ ብልፅግናን በማፋጠን ለጋራ ከፍታ ምቹ መሠረት ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ