
ባሕር ዳር: ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የጸጥታ አባላት የእውቅና መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) የፖሊስ ሠራዊቱ የአማራን ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት የመጠበቅ ኀላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ የገጠሙትን የጸጥታ ችግሮችም ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጋር በመኾን መሥዋትነት እየከፈለ አንጻራዊ ሰላም መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
ባለፉት ጊዚያት የፖሊስ ተቋሙ ሪፎርም ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል። የእውቅና እና የሽልማት መርሐ ግብሩም የሪፎርሙ አንዱ አካል መኾኑን ጠቅሰዋል።
በሕግ ማስከበር ሥራ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የፖሊስ መሪዎች እና አባላትም እውቅና እና ሽልማት መሰጠቱንም አንስተዋል።
“የእውቅና እና ማበረታቻው ለሁሉም የፖሊስ ሠራዊት የማንቂያ ደወል ነው” ብለዋል። ሁሉም የፖሊስ ሠራዊት የተጣለበትን ኀላፊነት በትጋት እንዲወጣ እውቅና እና ሽልማቱ የሚያነሳሳ ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት።
የእውቅና እና ሽልማቱ የክልሉን ፖሊስ ከታችኛው እስከ ከፍተኛ ስትራቴጂክ መሪነት ደረጃ ያሉትን እንደሚያጠቃልልም ነው የገለጹት። ይህም መተካካትን መሠረት ያደረገ መሪ ለማፍራት አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የክልሉን ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ለመጠበቅ፣ የሕግ ማስከበር ሥራን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም አንስተዋል። ያሉት።
የክልሉ ፖሊስ ሠራዊት ሙያዊ ሥነ ምግባርን በመላበስ በቁርጠኝነት እና በታማኝነት እስከ ሕይዎት መስዋዕትነት ድረስ በመክፈል ሰላምን የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የፖሊስ ሠራዊቱን እውቅና መሥጠት እና ማበረታታት ተቋርጦ የቆየ መኾኑን ጠቁመው በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
የፖሊስ ሠራዊቱ ፖለቲካዊ ወገንተኝነት እና ሃይማኖታዊ ጣልቃ ገብነትን በመጸየፍ ለሕዝብ የገባውን ቃል በታማኝነት መፈጸም ላይ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አሳስበዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
