የሳይበር ጥቃት ሉዓላዊነትን እስከ ማስደፈር የሚያደርስ ነው።

10
ባሕር ዳር: ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሰዎች የከፈቱትን ድረ ገጽ እና የተጠቀሙበትን ኮምፒዩተር ወይም ሞባይል ሳይዘጉ ይተዋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የግል መረጃዎች በሌላ አካል እጅ የመግባት ዕድላቸው ይሰፋል።
የግል መረጃዎች ብቻ ሳይኾኑ በኀላፊነት የያዙት እና የሚያውቁት የሕዝብ እና መንግሥት መረጃዎችም ለአደጋ የተጋለጡ ይኾናል፡፡
አቶ ታፈረ ዓባይ የመንግሥት ሠራተኛ ናቸው። ማኅበራዊ ሚዲያም ይጠቀማሉ፡፡ ስለ ሳይበር ጥቃት ስጋቶች ሲነገር እሰማለሁ፤ ችግር ግን ገጥሞኝ አያውቅም የሚሉት አቶ ታፈረ የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንታቸውንም ኾነ ኮምፒዩተራቸውን እንደማይቆልፉ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነግረውናል።
ከማላውቀው አካል የሚመጣልኝን መልዕክት ባለመቀበል እና የሚያዝዘኝን ባለማድረግ ግን እጠነቀቃለሁ ነው ያሉት።
ስለ ሳይበር ደኅንነት እና ተያያዥ ጉዳዮች የዘርፉን ባለሙያ አናግረናል፡፡ ባለሙያው በውጭ ቋንቋዎች እና ሥነ ጽሑፍ እና በኮምፒዩተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው።
የሳይበር ዓለምን በይነ መረብ (ኢንተርኔት) ያስተሳሰራቸው እንደ ስልክ፣ ማኅበራዊ ሚዲያ እና ሌላም አገልግሎት የሚሰጡ ሥርዓቶች እና ቁሶች ናቸው በማለት ይገልጿቸዋል፡፡
የሳይበር ደኅንነት ማለት ደግሞ ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶችን መከላከል እና ጥቃቱ ከደረሰ በኋላም በቀላሉ ማስተካከል የሚቻልበት ሥርዓት መዘርጋት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡
የሳይበር ጥቃት ያለፈቃዳቸው የግለሰቦችን መረጃ በማወቅ በማጭበርበር የሀገርን መረጃ የመስረቅ፣ የማዛባት እና እስከ ማውደም የሚደርስ አደጋ ነው ይላሉ፡፡ ውጤቱም የግለሰቦችን መረጃ፣ ሃብት፣ መልካም ሥም እና ክብር ከማጉደፍ እስከ የሀገር ምጣኔ ሃብትን ማውደም እና ማዛባት ይደርሳል ብለዋል፡፡
የሰዎችን የማንነት መለያ (Identity) መረጃዎችን ማወቅ የሚያስችሉ ሊንኮችን በመላክ ፎቶህ በኢንተርኔት ተለቋል ከፍተህ እየው፣ ሎተሪ አሸንፈሃል፤ የትምህርት ዕድል ተመቻችቷል የሚሉ ሀሰተኛ መልዕክቶች በስፋት ይስተዋላሉ ነው ያሉት፡፡
ሊንኮቹ ሲከፈቱ ግን ለሳይበር ጥቃት ያጋልጣሉ፡፡ ስለኾነም ከማይታመን አካል የሚላክ መልዕክት እና ሊንክን መክፈት አይገባም ብለዋል ባለሙያው፡፡
መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ:-
👉 ቶሎ ቶሎ የሚቀየር እና ጠንካራ የይለፍ ቃል (Pass Word) እና የሁለትዮሽ ማረጋገጫ ማመሳከሪያ (Two Factor Authantication) መጠቀም፣
👉 የግላዊነት ቅንብሮች (Privacy Settings) ላይ መረጃዎችን መወሰን፣
👉 ከማይታመን አካል የሚላኩ ማስፈንጠሪያዎችን (Links) አለመክፈት፣
👉 በአምራች ኩባንያዎች የታደሱ ( የወቅቱ ዝማኔ የተደረገላቸው) ሶፍትዌሮችን መጠቀም፣
👉 የግል አካውንትን ለሌላ አሳልፎ አለመስጠት እና ከተጠቀሙ በኋላ መውጣት (Log out)ማድረግ የሳይበር ደኅንነት ማስጠበቂያ ናቸው ነው ያሉት፡፡
የተቋማት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) የሥራ ክፍሎችም ግልጽነት በመፍጠር የተቋማቸውን የሳይበር ደኅንነት ማጠናከር መሠረታዊ ነገር ነው ብለዋል።
ባለሙያዎችም ለማኅበራዊ ምህንድስና ጥቃት እንዳይጋለጡ የምሥጢር ጠባቂነትን ሥነ ምግባርን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ዲጂታላይዜሽን እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት እየዘመነ ሲመጣ የሳይበር ጥቃቱም ስለሚወሳሰብ የደኅንነት ፖሊሲ አውጥቶ መተግበር ይገባል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኀላፊ የቻለ ይግዛው በጥቅምት ወር ዓለም አቀፍ የሳይበር ደኅንነት በንቅናቄ እየተከበረ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በሀገር ደረጃ ለ6ኛ ጊዜ የሚከበረው የሳይበር ደኅንነት በአማራ ክልልም በትኩረት እየተሠራበት ነው ብለዋል። ኅብረተሰቡ ዕውቀት እና ክህሎቱን እንዲያሻሽል መልዕክቶችን የማስተላለፍ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የሳይበር ደኅንነት ግለሰብን፣ ተቋምን እና ሀገርን የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ሰው በሳይበር አደጋ መረጃው ቢጠፋበት፣ ቢሰረቅ ወይም ኮምፒዩተሩ ቢበላሽ የሚኖረውን ኪሳራ ማሰብ ይገባል ነው ያሉት።
“በሳይበር ጥቃት ግለሰቦች መረጃቸውን ያጣሉ፣ ሌላ ሰው ይጠቀምበታል፣ ይህም በግለሰብም ኾነ በተቋም ደረጃ ችግር ይፈጥል፡፡ የሥም ማጥፋት፣ የምርት ሂደትን ማሰናከል፣ የሀገርን ገጽታ ማበላሸት እና ምጣኔ ሃብት አሳልፎ መስጠት፣ ሉዓላዊነትን እስከ መስጠት የሚያደርስ ከፍተኛ አደጋ ነውም ብለዋል፡፡
ይህንን ሀገራዊ የደኅንነት ዘርፍ ለመጠበቅ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባውም አመላክተዋል።
በየተቋማቱም ግንዛቤ መፍጠር፣ የሚለሙ ሲስተሞች ከመተግበራቸው በፊት የደኅንነት ፍተሻን ማድረግ እንደሚስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ለዚህም ተቋማት የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleስለትናንቱ ማመስገን ለነገው ማጀገን ነው።
Next articleበበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ86 ቢሊዮን ብር በላይ የመንግሥት እና የሕዝብ ሃብት ማዳን ተችሏል።