ከ2ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የምገባ ተጠቃሚ ይኾናሉ።

14
ባሕር ዳር: ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የትምህርት ቤት ምገባ በብዙ የዓለም ሀገራት ተተግብሮ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ መርሐ ግብር ነው።
መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያም በ2008 የትምህርት ዘመን በችግር ተጋላጭ በኾኑ የቅድመ መደበኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንደተደረገ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
መርሐ ግብሩ የተማሪዎችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ የጤና እና የሥነ ምግብ ሁኔታ ማሻሻል፣ በትምህርት ቤቶች የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሂደትን መፍጠር እና የሕጻናትን አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ደኅንነት ማስጠበቅ ዓላማ ያደረገ ነው።
መረጃው እንደሚያመለክተው መርሐ ግብሩ በሀገሪቱ ከተጀመረ ጀምሮ የተማሪ ማቋረጥን እና መድገም ምጣኔ ቀንሷል፤ የተማሪዎች ውጤትም እንዲሻሻል አድርጓል። የተማሪወችን የምግብ እና የጤና ሁኔታ በማሻሻል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከ ነው።
በአማራ ክልል በተለይም ድርቅ እና እርጥበት አጠር በኾኑ አካባቢዎች ከ1980ዎቹ ጀምሮ ደራሽ ምገባ ሲደረግ ቆይቷል፤ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በተደራጀ መንገድ እየተካሄደ ይገኛል።
በምገባ መርሐ ግብሩ ከታቀፉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰሃላ ወረዳ የመሽሃ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ነው።
በትምህርት ቤቱ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ወልዳት ደሳለኝ ላለፉት ስምንት ዓመታት ያህል በምገባ መርሐ ግብሩ ተጠቃሚ መኾኑን ነው የነገረን። ተማሪ ወልዳት ትምህርት ከመግባቱ በፊት በቤተሰብ አቅም ችግር የመማር ዕድሉን ማግኘት አልቻለም ነበር። ይልቁንም አብዛኛው ጊዜውን የሚያሳልፈው በሥራ ነበር።
ይሁን እንጅ በትምህርት ቤቱ ምገባ መጀመሩን ተከትሎ ባለሙያዎች በአካባቢው ትምህርት ያልገቡ ልጆች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲኾኑ በሠሩት ሥራ ወደ ትምህርት እንዲገባ አድርጎታል።
ወደ ትምህር ከገባ ጀምሮ ግን ለትምህርቱ በሰጠው ትኩረት በየዓመቱ ተሸላሚ ሊኾን ችሏል። በቀጣይም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለመቀላቀል የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መኾኑንም ነው የገለጸው።
የምገባ መርሐ ግብሩ በተለይም ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አቅም እንደኾናቸውም ነው የገለጸው።
በሰሃላ ወረዳ የመሽሃ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አማኑኤል በርሄ እንዳሉት በትምህርት ቤቱ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ድርጅቶች እና በመንግሥት ድጋፍ የትምህርት ቤት ምገባ እየተካሄደ ይገኛል።
የምገባ መርሐ ግብሩ በመጀመሩ በአቅም ችግር ሲያቋርጡ የነበሩ ተማሪዎችን በማስቀጠል የማቋረጥ ምጣኔ እንዲቀንስ ተደርጓል ብለዋል። የተማሪዎች የመከታተል እና የአቀባበል አቅም እየተሻሻለ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የተማሪዎች ውጤትም በፊት ከነበረው መሻሻሉን ነው የገለጹት። በ2018 የትምህርት ዘመንም በትምህርት ቤቱ 1 ሺህ 900 ተማሪዎች በምገባ መርሐ ግብሩ ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል።
አካባቢው በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭ በመኾኑ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥም ጠይቀዋል።
በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ባለሙያ መኮንን ታደሰ እንደገለጹት የትምህርት ቤት ምገባ በክልሉ በተለይም ደግሞ ድርቅ እና እርጥበት አጠር በኾኑ አካባቢዎች አሥርት ዓመታትን አስቆጥሯል።
ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በተደራጀ መንገድ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በዚህም የተማሪዎችን የመቅረት እና የማቋረጥ ምጣኔ መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
የተማሪዎችን ማቋረጥ ከመቀነስ ባለፈ የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል፣ ከክፍል ክፍል መዛወር እና ውጤታቸው እየተሻሻለ መምጣቱንም ነው የገለጹት።
በ2018 የትምህርት ዘመን የክልሉ መንግሥት 500 ሚሊዮን ብር ለትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር በጀት መመደቡን ባለሙያው ገልጸዋል። በቅርቡም ምገባ ይጀመራል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ አሁን ላይ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም የምግብ ፕሮግራም እየተደገፉ የሚገኙ 132 ሺህ ተማሪዎች ምገባ እየተደረገላቸው መኾኑን ገልጸዋል።
በትምህርት ዘመኑ በክልሉ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በምገባ መርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ይኾናሉም ተብሏል። የትምህርት ቤት ምገባን እንደ አንድ የትምህርት ግብዓት በመውሰድ ማኅበረሰቡ፣ ባለሃብቶች እና ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት ጉባዔውን ያካሂዳል።
Next articleስለትናንቱ ማመስገን ለነገው ማጀገን ነው።