በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስፋት እየተሠራ ነው።

5
ባሕር ዳር: ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በተመረጡ ከተሞች ተመርቆ ወደ አገልግሎት መግባቱ ይታወሳል።
በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት እስከ አሁን ድረስ የነበረውን አፈጻጸም የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በባሕር ዳር ከተማ ገምግሟል።
የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባንቻምላክ ገብረማርያም በክልሉ የአገልግሎት አሰጣጥን በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመሥጠት እና ዲጅታላይዝ በማድረግ የተሳለጠ እንዲኾን እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተደራጀ መልኩ ለሕዝቡ በሚገባ ማሳወቅ እንደሚጠበቅም አንስተዋል። ተቋማትም በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለይተው ማሳወቅ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
በአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሠሩ ሠራተኞች እና መሪዎች በዲሲፕሊን እንዲመሩ የሚያስችል የሥነ ምግባር መመሪያ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
እስካሁን የተገኙ ልምዶችን በማጠናከር እና ጉድለቶችን ገምግሞ በማስተካከል አገልግሎቱ እየሰፋ እንደሚሄድ ጠቁመዋል። “በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሠሩ ሠራተኞች የሚመሩበት የሥነ ምግባር መመሪያ ረቂቅ ቀርቦ” ውይይት ተደርጎበታል።
የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ ፈንታው ፈጠነ በማዕከሉ 13 የአገልግሎት ዓይነቶች ተለይተው እየተሰጡ መኾኑን ገልጸዋል። በቦታ እና በጊዜ ያልተገደበ አገልግሎት በመስጠት በኩል ለንግድ ሥርዓቱ ውጤታማ ነው ብለዋል።
በአገልግሎት ሰጭዎች በኩል የሚስተዋለውን ብልሹ አሠራር የሚያስቀር መኾኑንም አመላክተዋል። የንግድ አገልግሎት በርካታ ተቋማት የሚጠይቅ በመኾኑ ሁሉንም ተቋማት በአንድ ቦታ እንዲገኙ በማስቻሉ እንግልትን ያስቀረ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አበባ ጌታሁን የቢሮው አገልግሎቶች በማዕከሉ ተካትተው እንዲሰጡ መደረጉ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመሥጠት ማስቻሉን አንስተዋል። በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ብልሹ አሠራሮችንም የሚቀርፍ መኾኑን ነው የተናገሩት።
በቢሮው በኩል በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶች ተለይተው መሠጠታቸውን ገልጸው በቀጣይም እንደ ተቋም የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት ለመወጣት ቁርጠኛ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በውይይቱ እስከ አሁን ድረስ የተከናወኑ ተግባራት ቀርበዋል። በአገልግሎቱ መተግበር የተገኙ ውጤቶች እና ልምዶችም በውይይቱ ተነስተዋል። አገልግሎቱን ውጤታማ በኾነ መንገድ ለመስጠት እና ለማስፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያም ምክክር ተደርጓል።
በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሠሩ ሠራተኞች የሚመሩበት የሥነ ምግባር መመሪያ ረቂቅ ሰነድ ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የፖለቲካ ሥርዓታችን ማዘመን ይገባናል” አቶ አደም ፋራህ