
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) በመላው ዓለም ሰማይ ስር የኢትዮጵያን ሰንደቅ አዝሎ ከሚዞረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀጥሎ በማዕበል እና ወጀብ እየታገዘ በውኃማ አካል ላይ እንደ ቀስተደመና የሚዘረጋው የኢትዮጵያ ሰንደቅ በጣና ሐይቅ ላይ ነው፡፡
የጣና ሐይቅ በኢትዮጵያ በስፋቱ የቀዳሚነትን ስፍራ ይይዛል፡፡ በ3 ሺህ 672 ስኩየር ኪሎ ሜትር ላይ ተረጋግቶ የተዘረጋው የጣና ሐይቅ ከሰሜን ወደ ደቡብ 84 ኪሎ ሜትር እና ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ደግሞ 66 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው፡፡ ከ9 እስከ 14 ሜትር ጥልቀት እንዳለው ደግሞ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተደጋጋሚ የቀረቡ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
ጣና ሐይቅ ለኢትዮጵያውያን ውኃ ብቻ ሳይሆን በመከራ ዘመን መሸሸጊያ፣ በጨለማ ዘመን ብርሃን፣ በውጣ ውረድ ጊዜ ድልድይ ሆኖ አገልግሏል፡፡ የኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ በድርሳናት ይመሳከር ቢባል ዋቢ እና ዋስ ከሚሆኗት መካከል በጣና ሐይቅ ገዳማት የሚገኙት ዕድሜ ጠገብ ቅርሶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ጣና ሐይቅ ውስጥ ካሉት 44 የሚደርሱ ገዳማት ውስጥ አሁን ላይ ከሃያ ስድስቱ መናኒያን እና ገዳማውያን፣ ታቦታት እና ካህናት እንደሚኖሩባቸው ይነገራል፡፡
በጣና ሐይቅ ውስጥ ካሉት ገዳማት ቀደምት እንደሆነ የሚነገርለት የጣና ቅዱስ ቂርቆስ አባቶች እና እናቶች አንድነት ገዳም ከክርስቶስ ልደት በፊት በ982 ዓ.ዓ ገደማ እንደተመሠረተ ይነገራል፡፡ የጣና ቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ኢትዮጵያ ከኦሪት ዘመን ጀምሮ ያላትን ታሪክ ጠብቆ ያቆየ ገዳም ነው፡፡ ገዳሙ በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተው የእምቦጭ አረም ለኅልውናው ስጋት ከፈጠረበት ቆይቷል፡፡
‘‘ገዳሙ በዚህ ጊዜ ከ200 በላይ መነኮሳት እና ከ50 በላይ የአብነት ተማሪዎች አሉት’’ ያሉት የገዳሙ አፈ መምህር አባ ኪዳነማርያም ገብረማርያም ‘‘እምቦጭ በገዳማውያኑ ብቻ ሳይሆን በገዳሙ ኅልውና ላይም አደጋ ፈጥሯል’’ ነው ያሉት፡፡
በሐይቁ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የበቀለው የእምቦጭ አረም በነፋስ እየተገፋ በገዳሙ የግጦሽ እና የማሳ መሬት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ በአዝመራ እና በግጦሽ መሬት ላይ ጉዳት ስለሚያደርስ ለዘመናት እራሱን ችሎ የኖረው ገዳሙ እና ገዳማውያኑ ለዕርዳታ እጃቸውን እየዘረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የገዳሙ አፈ መምህር የሀብት እና ዕውቀት ፀጋ ያለው ሁሉ ገዳሙን እንዲታደግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ለገዳሙ የእርሻ ማሳ የጋቢዮን አጥር ቢቀርብ በአዝመራቸው ላይ አደጋው ስለሚቀንስ በሐይቁ ክፍል ላይ ያለውን አረም ለማስወገድ ጊዜ እና አቅም እንደሚኖራቸውም ገልፀዋል፡፡
በሐይቁ ላይ የተከሰተውን መጤ አረም ለማስወገድ መናንያኑ ያለዕረፍት እየሠሩ ነው፡፡ ‘‘ቦታው ሲኖር ሰው ይኖራል፤ ሰው ካለ ደግሞ ታሪክ ተጠብቆ ይዘልቃልና ለታሪካችን ስንል ቦታውን እንታደግ’’ ያሉት አባ ኪዳነማሪያም የተለያየ የኅብረተሰብ ክፍሎች አረሙን ለማስወገድ ላለው እንቅስቃሴም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ፎቶ፡- ከድረገጽ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡