
ባሕር ዳር: ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከበርካታ ችግሮቻችን መካከል አንዱ የሕዝብ እና የመንግሥት ሃብት እና ንብረትን እንደ ግል ንብረታችን ያለማየታችን ነገር ለኔ ይታየኛል፡፡
አንዳንድ ባለጸጋዎች ከትንሽ ገንዘብ እና ሥራ ጀምረው ጠንክረው በመሥራት እና በመቆጠብ ለባለሃብትነት እንደደረሱ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ እንደ ጃፓን ያሉ ሀገራት ደግሞ ሀገራዊ ልማታቸው ከዜጎቿ ጥብቅ ዲሲፕሊን ጭምር እንደተገኘ ይነገራል፡፡
ግለሰቦች ጠንክረው ሠርተው፣ ቆጥበው እና በአግባቡ ተጠቅመው ለብልጽግና ከበቁ ማኅበረሰብስ ለምን ተመሳሳዩን አይተገብርም የሚል ሃሳብ ማንሳት ይገባል፡፡
ከሰፈር እስከ ፌዴራል ድረስ በሚገኙ የሕዝብ እና የመንግሥት ንብረቶች ላይ ያለው የአያያዝ እና የአጠቃቀም ብክነት የድህነታችን አንዱ ምሰሶ እንደኾነ አምናለሁ፡፡
በቤታችን የምንገለገልባቸውን የመብራት፣ የውኃ እና ሌሎችም ምን ያህል እንደምንቆጥባቸው እናውቀዋለን፡፡ ችግሩ ግን እነዚህን እና መሰል ንብረቶችን በወል በምንጠቀምበት ጊዜ ያለን አባካኝነት ነው፡፡
በቢሯችን የኤሌክትሪክ፣ የውኃ፣ የተሽከርካሪ፣ የነዳጅ፣ የኮምፒዩተር፣ የጽሕፈት መሣሪያዎች አጠቃቀም እናስተውል፡፡
አንድ የኮምፒዩተር ወረቀት በሱቅ እስከ አምስት ብር ድረስ ይሸጣል። ይህን ቀለል አድርገን ልናስብ ብንችልም በቢሯችን ምን ያህል ወረቀት በግዴለሽነት እንደምናባክን እራሳችን ብንጠይቅ ክፍተታችን ብዙ ነው፡፡
ይህን ስል ስስታም፣ አስተሳሰበ ትንሽ፣ አይቶ አያውቅ እና የመሳሰሉት ትችቶች እና ነቀፌታዎች ገጥመውኝ ያውቃሉ፡፡ ይህም ተማርኩ የሚለው ሳይቀር ምን ያህል ግዴለሽ እና አባካኝ መኾኑን ነው ያረጋገጠልኝ፡፡
የማኔጅመንት አባል ኾኜ እሠራበት በነበረው አንድ መሥሪያ ቤት ውይይት የሚደረግባቸውን ርዕሰ ጉዳች እና እቅዶችን አርቅቆ ለ10 አባላት ቀድሞ የማድረስ ሥራ እሠራ ነበር፡፡ ውይይት ከተደረገበት በኋላም የሚሰጡ አስተያየቶች እና ማስተካከያዎች ተጨምረው እንደገና ይጻፋል፡፡
ስለኾነም ለመወያያ ለሚቀርበውን ረቂቁ በአንድ ገጹ በተጻፈበት ወረቀት አዘጋጅቼ አቀረብኩ፡፡ የተቋሙ ኀላፊ እንደ ወረደ ማሰብ እንደሌለብኝ እና በድጋሚ እንደዚያ ባለ ወረቀት ረቂቅ እንዳላቀርብ መከረኝ፡፡
እኔም ትዕዛዙን ተቀብየ ለሚሻሻል ሃሳብ የማዘጋጀውን ጽሑፍ በአዲስ ወረቀት እየጻፍኩ ለአንድ እና ሁለት ርእሰ ጉዳዮች ደስታ ወረቀቶችን ለ4 ዓመታት ያህል ስናባክን ኖርን ማለት እችላለሁ፡፡
አስቡት! ያ ተቋም የግል ቢኾን ኖሮ እንደዚያ በአባካኝነት እንጠቀም ነበር ወይ?
በየቢሯችን ያሉ ኮምፒዩተሮችን በአግባቡ ባለመዝጋት ለጥራት ቅነሳ (Deprecation) አላስፈላጊ መብራቶችን ባለማጥፋት፣ ውኃ በማባከን፣ ተሽከርካሪ እና ነዳጅ አላግባብ በመጠቀም፣ ሌችም በቢሮ ውስጥም ኾነ በውጭ የሚገኙ የሕዝብ ሃብቶችን በማባከን በኩል ድርሻችን ከፍተኛ ነው፡፡
አንዳንዶች የሕዝብም እንበለው የመንግሥት ሃብቱ የሀገር መኾኑን ተረድተው በቁጠባ እና በአግባቡ ሲጠቀሙ እና ሲመክሩ “የኛ ተቆርቋሪ”፣ “የኛ የመንግሥት አሳቢ”፣ እና በመሰል ሽሙጦች ማሸማቀቅም ከአባካኝነታችን ጋር የተዋሐደን አመለካከትም አለብን፡፡
እንደ ደም ሥር የሚያዩትን በጀት እና ነዳጅ ካልኾነ በስተቀር በሌሎቹ የሃብት ብክነቶች ላይ ኀላፊነት ያለባቸው የማይመስላቸው ኀላፊዎችም እንዳሉ እታዘባለሁ፡፡ አበል፣ ደመወዝ፣ ግዢ ሲጠየቁ በጀት አለመኖሩን የሚናገሩትን ያክል በመጋዘን ውስጥ ኾነው የሚባክኑ ንብረቶች በጀት መኾናቸውን ግን ባላየ ያልፉታል፡፡
አከራይ እና ተከራይ በመብራት፣ ውኃ እና መጸዳጃ ቤት አጠቃቀም ግንኙነት፣ ግቢያችን የምናጸዳበት እና ጎዳናዎችን የምናቆሽሽበት የኀላፊነት ጉድለት፣ ለግል መኪና እና ነዳጅ የምናደርገው ቁጠባ ከመሥሪያ ቤት መኪና አጠቃቀማችን ጋር ሲነጻጸር አሁንም ትልቅ የኀላፊነት መጓደል እና ብክነት ያለበት ነው እላለሁ።
በቤታችን አስቤዛ አለቀ፤ አላለቀ እያልን የምንሳቀቀው እና ምን ጊዜ ጨረስሽው እያልን ሴቶቻችን የምናስቸግረውን ያህል በቢሯችንም ኾነ በአደባባዮች ለሕዝብ እና ሀገር ሃብት ጠንቃቃ እና ቆጣቢ መኾን ብንችል ክፋቱ ምን ላይ ነው?
ሁሉንም ሃብት እና ንብረት በቁጠባ በመጠቀም ድህነትን መታገል እና ማሸነፍ እንጂ እያባከኑ ጨምሩልኝ ማለት የትም እንደማያደርሰን መገንዘብ ይገባናል ባይ ነኝ፡፡ አንዳችን ስንቆጥብ ሌላችን እያባከንም ለውጥ አናመጣም፡፡
እናም ውስን ሃብትን እንደ ግል ንብረት በቁጠባ በመጠቀም ልማታችን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡
እኛ ቆሻሻ ብለን የምናቃጥለው ወረቀት ለድሃ ልጆች ጥሩ መጻፊያ ኾኖ እንደሚያገለግል መረዳት አለብን፡፡ እኛ በቅንጦት ወይም ባለማስተዋል ሌላ እየተመኘን የምናባክነው ሃብት በሕዝብ ሥም የተገኘ እርዳታ፣ ብድር ወይም ከሕዝብ የተሰበሰበ ግብር መኾኑንም እናስብ እላለሁ፡፡
ሰላም!
በዋሴ ባዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
