የተከበሩ የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ

7
ባሕር ዳር: ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተከበሩ የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ጥቅምት 12/1925 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ አንኮበር ከተማ ነው የተወለዱት፡፡ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ገና በልጅነታቸው የሒሳብ እና የስዕል ችሎታ እንደነበራቸው ይነገራል፡፡
ገና በ15 ዓመታቸው ለምህንድስና ትምህርት ወደ እንግሊዝ ሀገር ተልከው የስዕል ትምህርት ቤት ውስጥ ገብተው ተማሩ፡፡ በማዕከሉም የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተማሪ ኾነዋል፡፡ በቀለም ቅብ ቅርጻ ቅርጽ እና በኪነ ሕንጻ ጥበብ ተመርቀዋል፡፡
ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የኢትዮጵያውያንን ታሪክ እና ባሕል አጥንተዋል፡፡ በ1946 ዓ.ም በ22 ዓመታቸው የተለያዩ የሥነ ጥበብ ሥራዎቻቸውን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አቅርበዋል፡፡ ሁለቱን ስዕሎቻቸውን ንጉሱ አጼ ኃይለሥላሴ እንደገዟቸውም ይነገራል፡፡ በሌሎች ሀገራትም ስዕሎቻቸውን ማቅረባቸውን ታሪካቸው ያወሳል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሥነ ጥበብ ከፍተኛ ሽልማትን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ90 በላይ ሜዳሊያ፣ ሽልማቶች እና የክብር ዜግነትንም አግኝተዋል፡፡
ሐምሌ 1997 ዓ.ም በአየርላንድ በተደረገ 30ኛው ዓለም አቀፍ የኪነ ጥበብ ባሕል እና ሳይንስ ዓለም አቀፍ በዓል ላይ ዘ ኢንተርናሽናል ባዮግራፊካል ሴንተር ኦፍ ካምብሪጅ የተባለው ተቋም በሥነ ጥበብ የመጨረሻ ሽልማት የኾነውን የዳቪንቼ አልማዝ የተባለውን ከፍተኛ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ ሽልማትም ብቸኛው አፍሪካዊ የሥነ ጥበብ ሰው ኾነዋል፡፡
በዚሁ ዝግጅት ላይም ዘ ዩናይትድ ካልቸራል ኮንቬንሽን ኦፍ ዘ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ኢንተርናሽናል ፒስ ፕራይስ ልዩ ሽልማት እና የክብር የሰላም አምባሳደርነትንም ሰጥቷቸዋል፡፡ ሚያዚያ 2004 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የተወለዱት ጥቅምት 12/1925 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ነበር፡፡
ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ጋዜጣ
✍️ ዓለምን ከጨለማ ያወጣው የፈጠራ ሊቅ
ቶማስ አልቫ ኤዲሰን እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን የካቲት 11/1847 ሚላን፣ ኦሃዮ ውስጥ ነው የተወለደው። ኤዲሰን ሰባተኛው እና የመጨረሻው የሳሙኤል እና ናንሲ ኤሊዮት ኤዲሰን ልጅ ነበር። የትምህርት ዘመኑን የጀመረው ገና በልጅነቱ ነበር። ነገር ግን መምህራኑ “ትኩረቱን መሰብሰብ የማይችል ልጅ በማለት ይፈርጁት እንደነበር ታሪኩ ላይ ተቀምጧል።
በዚህ ምክንያት በትምህርት ቤት የቆየው ለጥቂት ወራት ብቻ ሲኾን፣ እናቱ ናንሲ የቀድሞ አስተማሪ ስለነበረች ከመደበኛ ትምህርት ቤት አውጥታ በቤት ውስጥ ማስተማር ጀመረች።ይህ የቤት ውስጥ ትምህርት ለኤዲሰን ትልቅ ዕድል ኾነለት። በተናጠልም ኾነ በጋራ በዓለም የተመዘገቡ 1 ሺህ 93 የፈጠራ ባለቤትነት መብቶችም አሉት፡፡
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1863 በቴሌግራፍ ኢንዱስትሪ ሥራውን የጀመረው ኤዲሰን በጥር 1879 ደግሞ የመጀመሪያውን ከፍተኛ የመቋቋም ችሎታ ያለውን ኤሌክትሪክ መብራትን ፈጠረ፡፡ መብራቱ ለጥቂት ሰዓታት ብቻ ቆይቶ ተቃጥሏል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ቁሶችን ሞክሮም ሳይሳካለት ቆይቷል፡፡
ሥራውን ጠንክሮ መሥራትን እና ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅም አምኗል፡፡ እናም ከ6 ሺህ ያላነሱ ሙከራዎችን ማድረጉም ይነገራል፡፡
“እኔ ራሴ ተስፋ አልቆረጥኩም ወይም ለስኬት ተስፋ የቆረጥኩበት ጊዜ የለም” በሚለው አባባሉ የሚጠቀስለት የፈጠራ ሰው ከብዙ ጥረቱ እና ከብዙ ምርምር፣ ከበርካታ ሙከራ እና የገንዘብ ወጭ በኋላ የተሞከረው አምፖል ለ40 ሰዓታት የበራበት ስኬት ተገኘ፡፡ ይህም የፈጠራ ሥራው የተሳካበት ጊዜ እ.ኤ.አ በጥቅምት 11/1872 ነበር፡፡
ምንጭ፦ ብሪታኒካ እና ባዮግራፊ ድረ ገጾች
✍️ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምሥረታ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ሶቪየት ኅብረት እና ቻይናን ጨምሮ በ51 መንግሥታት ነው የተቋቋመው።
የዓለምን ሰላም ማስጠበቅ እና የዓለም አቀፍ ሕግን ማስከበር ዓላማ ያለው ድርጅት ነው፡፡ አሁን ላይ ከ190 በላይ ሀገራት የድርጅቱ አባል ናቸው። የጋራ እርምጃ በሚያስፈልግበት ወቅት ዓለም አቀፍ ችግሮችን የመፍታት ተልዕኮ እና መድረሻ አለው።
ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ ወይም የሰብዓዊነት ተፈጥሮ ያላቸውን ችግሮችን ለመፍታት፤ እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች እና መሠረታዊ ነጻነቶች መስፋፋትን እና በዘር፣ በጾታ፣ በቋንቋ ወይም በሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ ለሁሉም ሰው እንዲከበሩ የሚያስችል ዓለም አቀፍ ትብብርን ማረጋገጥ ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተፈጠረው ወደፊት የሚመጡትን የዓለም ጦርነቶች ለመከላከል እና ዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ነው። ሰብዓዊ መብቶችን ለመጠበቅ፣ ሰብዓዊ እርዳታ ለመስጠት እና ዓለም አቀፍ ሕግን ማስከበርም ዋና ተግባሩ ነው።
ዛሬ ላይ የምዕራባውያን የበላይነት አለበት በሚል የሚተቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የተመሠረተው እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን ጥቅምት 14/1938 ነበር፡፡
ምንጭ፡- የተባበሩት መንግሥታት ድረጅት ድረ ገጽ
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጎል ኢትዮጵያ ለመተማ ጠቅላላ ሆስፒታል ድጋፍ አደረገ።
Next articleየሕዝብ ሃብትን እንደግላችን ብናይስ?