
ገንዳ ውኃ:ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ጎል ኢትዮጵያ የተሠኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት በምዕራብ ጎንደር ዞን ለመተማ ጠቅላላ ሆስፒታል ድጋፍ አድርጓል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ዮሴፍ ጉርባ ጎል ኢትዮጵያ ለመተማ ጠቅላላ ሆስፒታል ላደረገው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።
የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ ወደ ዞኑ ለማስገባት በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ እንቅፋት መኾኑን ተናግረዋል።
በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ሥራዎች በጋራ እየተሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ እንዳለበትም ተናግረዋል። ቀጣይም ሌሎች ረጅ ድርጅቶች የጤናውን ዘርፍ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የመተማ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ሞገስ አዲስ ጎል ኢትዮጵያ በሆስፒታሉ የታካሚዎችን አገልግሎት ለማፋጠን የመድኃኒት አቅርቦት ድጋፍ ማድረጉን እና ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ የመፀዳጃ ቤት ግንባታን አስገንብቶ ማስረከቡን ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ ማነቆ የኾኑ ችግሮችን ለመፍታት እና የማኅበረሰቡን የሕክምና እንግልት ለመቀነስ ጎል ኢትዮጵያ እያደረገ ያለው በጎ ተግባር የሚበረታታ መኾኑንም አብራርተዋል።
ሆስፒታሉ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማኅበረሰብ እንደሚያገለግል የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ ይህን ቁጥሩ ከፍተኛ የኾነ ማኅበረሰብ ለማስተናገድ የመድኃኒት አቅርቦት፣ የስፔሻሊስት ዶክተሮች እጥረት እና ሌሎች መሰልች ችግሮች ማነቆ እንደኾኑም አስረድተዋል።
ችግሮችን ለመፍታትም ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነውም ብለዋል።
የጎል ኢትዮጵያ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሥራ አሥኪያጅ ተወካይ አስራት መኮነን ጎል ኢትዮጵያ ከሆስፒታሉ ጋር በመተባበር የሆስፒታሉን ጫና ለመቀነስ እና በተሻለ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ ጥረት እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
ድርጅቱ የሆስፒታሉን የጤና ክፍተት በመለየት፣ ደረጃውን የጠበቀ የመፀዳጃ ቤት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ገንብቶ ማስረከቡን ገልጸዋል።
የሆስፒታሉን የመድኃኒት እጥረት ለመቅረፍ ድርጅቱ
ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል።
ቀጣይም ጎል ኢትዮጵያ ከሆስፒታሉ ጋር በተቀናጀ መንገድ ክፍተቶችን በመለየት የተሻለ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
