
ደሴ:ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በዞኑ ለሚገኙ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወረዳዎች ዘመናዊ አምቡላንስ፣ የሕክምና ቁሳቁስ እና የመድኃኒት ድጋፍ አድርጓል፡፡
በኢትዩጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መላኩ ቸኮል ማኅበሩ ከአጋር ድርጅቶች ባገኘው ድጋፍ ከ76 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ለተንታ እና ለሌጋምቦ ወረዳዎች ዘመናዊ አምቡላንስ፣ የሕክምና ቁሳቁስ እና መድኃኒት ድጋፍ አድርጓል፡፡
ለጃማ ወረዳ ደግሞ የሕክምና ቁሳቁስ እና የመድኃኒት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው በለጠ ቀይ መስቀል ያደረገው ድጋፍ የሕክምና ተቋማት ለታካሚዎች ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ የእናቶችን እና የሕጻናትን ጤና ለመጠበቅ ድጋፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን የሕክምና ተደራሽነትን ለማሳደግ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
አጋር አካላት የሚያደርጉት ድጋፍ የጤና አገልግሎትን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና አለው ነው ያሉት፡፡
ቀይ መስቀል ዛሬ ያደረገው ድጋፍ የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ የሚያስችል እንደኾነም ጠቁመዋል።
ድጋፍ የተደረጉት አምቡላንሶች የጤና እክል የደረሰባቸውን ዜጎች ፈጥኖ ወደ ሕክምና ተቋም ለመውሰድ እንደሚያስችሉ ገልጸዋል። የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፉም ጤና ጣቢያዎች ያለባቸውን የሕክምና ቁሳቁቁስ ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ:- ሠይድ አብዱ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
