ለአርሶ አደሮች ሰፊ የውኃ አማራጭ በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ይገባል።

2

ደባርቅ:ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ የተፈጥሮ ሃብት እና ተፋሰስ ልማትን አስመልክቶ የንቅናቄ መድረክ በደባርቅ ከተማ አካሂዷል።

የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ለአርሶ አደሮች ሰፊ የውኃ አማራጭ በመፍጠር እና አማራጮችን በአግባቡ በመጠቀም ተጠቃሚነትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

በዞኑ በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ ጥሩ ተሞክሮ መኖሩን ገልጸዋል። በቀጣይ ሰፊ ተደራሽነትን እና ዘላቂነትን ለማረጋገጥ በትኩረት መሠራት አለበት ብለዋል።

የልማት ተግባራቱን ለማከናዎን ብቻ ሳይኾን በዘላቂነት ለመጠበቅ የኅብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ በመኾኑ የሕዝብ የባለቤትነት ስሜትን መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።

የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው አዳነ በተያዘው በጀት ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከ1 ሺህ 600 ሄክታር በላይ በሰብል ለመሸፈን ታቅዷል ብለዋል።

በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ደግሞ 627 ሺህ ችግኝ ለማፍላት መታቀዱንም አብራርተዋል። እነዚህንም ተግባራት ለመከዎን ይረዳ ዘንድ የግብዓት አቅርቦት ሥራዎች እየተከናዎኑ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ፣ የማሳ ልየታ እና ሌሎች ቅድመ ተግባራት መከናዎናቸውንም አብራርተዋል።

የተፈጥሮ ሃብት እና ተፋሰስ ልማት ሥራዎች ዘላቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተቋም ግንባታ ሥራዎችን በስፋት ለማከናዎን መታቀዱንም ጠቁመዋል።

በዞኑ ከ426 በላይ የተፈጥሮ ሃብት እና የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የሚከናዎኑበት ቦታ መኖሩን የገለጹት ኀላፊው ከ196 በላይ የሚኾኑት የልማት ቦታዎች ሞዴል እንደኾኑ ገልጸዋል።

የልማት ሥራዎቹን ዘላቂነት ከሚፈትኑ ችግሮች መካከል የልቅ ግጦሽ አንዱ ነው ብለዋል። ችግሩን ለመቅረፍ ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር የመኖ አቅርቦት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ዕቅዱን ለማሳካት እና ማኅበረሰባዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የአዳርቃይ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሹምዬ ነጋሽ በወረዳው ያለውን ውስን የውኃ ሃብት በመጠቀም የተለያዩ የሰብል፣ የአትክልት እና የፍራፍሬ ልማት ሥራዎችን እያከናዎኑ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

በሰብል ልማት ስንዴን፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት የማንጎ እና ቡና ልማት ሥራዎችን በስፋት እያለሙ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የጃናሞራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሷሊህ ሃሰን በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች ዘላቂነትን ማረጋገጥ እና የሕዝብ ባለቤትነት ስሜትን በመፍጠር በኩል አበረታች ተግባራት ማከናዎናቸውን ተናግረዋል።

ይሄን መልካም ጅምር አጠናክሮ ለማስቀጠልም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የጋራ መግባባት መደረሱንም አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየበጋ ስንዴ ልማት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።
Next article“የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ እናሳካዋለን” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ