
ጎንደር: ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በየዓመቱ ለውጥ እያሳየ እና አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
በ2017 የምርት ዘመን በበጋ መስኖ ስንዴ 574 ሄክታር መሬት በማልማት 22 ሺህ ኩንታል ምርት መገኘቱን የተናገሩት የከተማ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበራ አደባ ናቸው።
በ2018 ዓ.ም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 600 ሄክታር መሬት በማልማት ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ወደ ሥራ መገባቱን ነው የገለጹት።
ከ8 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ከተማዋ የማጓጓዝ ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ተናግረዋል። ለአርሶ አደሮች ለማሠራጨትም በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል። ለአልሚዎች የሚያጋጥመውን የነዳጅ አቅርቦት ለማሟላት ከአጋር ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
አርሶ አደሮችን በቅርበት በመደገፍ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠሩ የውይይቱ ተሳታፊ የቀበሌ ግብርና ባለሙያዎች ገልጸዋል።
“የውይይቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮች መሬታቸውን ደጋግመው በማረስ እና በማለስለስ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን” ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውጤታማ እንደነበሩም አስታውሰዋል።
በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 2 ሺህ 400 አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉም በውይይቱ ተገልጿል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
