
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛው ዙር ሞርጫ 13ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ጉባኤን እያካሄደ ነው፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጌትነት እውነቱ (ዶ.ር) ባሕር ዳር ከተማ በአሁኑ ጊዜ ፈጣን ልማት በማካሄድ ላይ እንደምትገኝ ተናግረዋል።
ኮሪደር ልማቱ የባሕር ዳር ከተማን ተፈጥሮ የገለጠ ብለዋል። ተጨማሪ ውበት የፈጠረ እና የቱሪስት ከተማነቷን በጉልህ ያሳየ ተግባር መኾኑንም ተናግረዋል። ይህም ለከተማዋ ነዋሪዎች ልዩ ደስታን የፈጠረ ተግባር እንደኾነ ነው የገለጹት።
የባሕር ዳር ከተማ ሰላም መኾን ነዋሪዎች በሰላም ወጥተው ሥራቸውን እንዲሠሩ ያስቻለ መኾኑንም ገልጸዋል። ሕዝቡ ልማቱን እና ሰላሙን በባለቤትነት ስሜት መጠበቅ ይገባዋልም ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ተጀምረው የነበሩ ፕሮጀክቶች የተጠናቀቁበት መኾኑንም ገልጸዋል። አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተጀምረው በጥብቅ አሠራር በመመራት ውጤት ላይ መድረሳቸውንም ተናግረዋል።
በሕገ ወጥ መንገድ በቤት ማኅበር ስም በመደራጀት ሊዘረፉ የነበሩ አካላትን በማስቀረት የከተማዋን ቦታ ከመዘረፍ በማዳን ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል መደረጉንም ገልጸዋል።
በኢንቨስትመንት ስም ቦታ ወስደው ለረጅም ዓመታት አጥረው ሳያለሙ ያስቀመጡ ግለሰቦች ቦታ ተነጥቆ ወደ ከተማ የመሬት ባንክ ገቢ የኾነበት ተግባር መከናወኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ውሳኔዎች ሲወሰኑም ውስብስብ ችግሮች የታለፉበት እንደነበር አንስተዋል።
በዚህ ተግባርም የሥራ መሪዎች ለከተማዋ ልማት እና ሰላም መኾን ቁርጠኝነት ያሳዩበት ተግባር መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ ለሚኖሩ ዜጎች የከተማ አሥተዳደሩ የዘረጋው አዲስ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር ተግባርም በመልካም የሚታይ ነው ብለዋል።
አሁንም ሕገ ወጥ ተግባር እንዳይፈጸም ጥብቅ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
የባሕር ዳር ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቅርቡ መጀመሩንም ተናግረዋል። አገልግሎቱ የከተማዋን ነዋሪዎች የሚፈልጉትን አገልግሎት በፍጥነት እና በቀላሉ ማግኘት ያስችላቸዋል ነው ያሉት፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባለፈው በጀት ዓመት በሠራው ከፍተኛ የልማት ተግባር በክልሉ ካሉ ከተሞች ጋር በመወዳደር 1ኛ ደረጃ በመውጣት ሽልማት ያገኘበት በጀት ዓመት እንደነበርም ጠቅሰዋል።
በክፍለ ከተማ ደረጃ ያሉ ምክር ቤቶች ጉባኤዎቻቸውን በተሟላ ሁኔታ በማካሄድ የከተማዋን ሰላም፣ ልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራትን እየገመገሙ በመምራት የተጀመረው ልማት እንዲሰፋ፤ የከተማዋ ሰላም እንዲጸና አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡
የባሕር ዳር ከተማ የምክር ቤት አባላት እና መላው የከተማዋ ነዋሪዎች ለልማቱ መሳለጥ እና ከተማዋ ሰላም እንድትኾን ላደረጉት ሁለንተናዊ ድጋፍም አመስግነዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
