
ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 118ኛው የሠራዊት ቀን “የማትደፈር ሀገር፣ የማይበገር ሠራዊት” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ብርሃን ከተማ እየተከበረ ነው።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ሠራዊቱ በክልሉ የገጠመው የጸጥታ መደፍረስ ችግር እንዲቀለበስ ያደረገ ጀግና መኾኑን ገልጸዋል። ሠራዊቱ የሕዝብ ልጅ በመኾኑ የከተማው ማኅበረሰብ ትልቅ ክብር እየሰጠው እንደኾነም አንስተዋል።
ሠራዊቱ ትልልቅ ሀገራዊ አጀንዳዎች በስኬት እንዲጠናቀቁ የማድረግ ሚናውን በብቃት እንዲወጣ የአካባቢያችንን ዘላቂ ሰላም መጠበቅ ከሕዝብ ይጠበቃል ብለዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጠላቶች ሊደፍሯት ቢፈልጉም በሠራዊቷ ቆራጥ ተጋድሎ ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ ለዛሬ ደርሳለች ብለዋል።
የዘንድሮው የሠራዊት ቀን ሲከበር ትልቅ ሀገራዊ ኩራት የኾነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተጠናቀቀበት ማግስት መኾኑ ለዓለም ሕዝብ ልዩ ትርጉም የሚሰጥ እንደኾነም ነው የገለጹት።
የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪዎችን ግብዓተ መሬት እየፈጸምን የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት እያስጠበቅንም ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮዎችን በብቃት መፈጸም እንዲችል የአሸናፊነት ሥነ ልቦና የተገነባ መኾኑንም ተናግረዋል።
ሌሎች እንዲኖሩ ሕይወቱን ከፍሎ ሀገር እና ሕዝብን የሚያስቀጥል፣ ሀገራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች እንዲሳለጡ የሚያደርግ ትልቅ ተቋም መኾኑንም አብራርተዋል። ሠራዊቱ የብሔራዊ ጥቅም ማስከበሪያ ቁልፍ መሣሪያ እንደኾነም ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ዳር ድንበር ከማስከበር አልፎ በሌሎች ሀገራት ጭምር ሰላም የማስከበር ተልዕኮውን በብቃት የተወጣ እና እየተወጣ ያለ፤ የተደራጀ ሠራዊት መኾኑንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት የመኾን ሕጋዊ እና ፍትሐዊ ጥያቄ አላት ያሉት ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ ዛሬም የውስጥ ባንዳዎችን እና ታሪካዊ ጠላቶችን አደብ በማስገዛት ሀገራዊ አጀንዳው እንዲሳካ ሠራዊቱ በተለመደው የጀግንነት ወኔ እና በልዩ ትኩረት ይሠራል ብለዋል።
በበዓል አከባበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የሰሜን ሸዋ ዞን እና የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
