የውል እርሻ ለምርት እና ምርታማነት ማደግ ድርሻው የጎላ ነው።

3

ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር” በግብርና ውል አርሻ” አሠራር ዙሪያ በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ.ር) የግብርና የውል እርሻ በኢትዮጵያ የቆየ አሠራር ቢኾንም በሕግ ማዕቀፍ ባለመታገዙ በአሠራር ሂደቱ ላይ እንቅፋት ፈጥሮ ቆይቷል ብለዋል። ችግሩን ለመፍታት ከ2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ የውል እርሻ አዋጅ በማጽደቅ ወደ ሥራ መገባቱንም ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት አዋጁ የአርሶ አደሮችን ምርት እና ምርታማነት እንዲያሳድጉ አድርጓል፤ አስመጭ እና ላኪዎች የሚፈልጉትን ምርት በጥራት እና በተፈለገው ጊዜ እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሯል። ለኢንዱስትሪዎችም ጥራት ያለው ምርት ለማቅረብ እያገዘ መኾኑንም አንስተዋል።

የውል እርሻ ከሰብል እና ከሆርቲ ካልቸር ባለፈ የተፈጥሮ ሃብት እና የእንስሳት ሃብቱን ጭምር እንደሚያካትትም ገልጸዋል። አሠራሩን እስከ ታች ድረስ ማስተዋወቅ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬው ተገኘ (ዶ.ር) የግብርናው ዘርፍ በባሕላዊ አሠራርም ቢኾን ከሀገራዊ ጥቅል ምርት 32 በመቶ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። ኢንስቲትዩቱ ባሕላዊውን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

እየሠራቸው ከሚገኙ ሥራዎች ውስጥም በውል እርሻ አሠራር ምርታማነትን ማሳደግ አንዱ እንደኾነ ነው የገለጹት።

አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም የሚያመርቱትን ምርት ከመካፈል ወጥተው እሴት ጨምረው ለገበያ እንዲያቀርቡ ማድረግ የቀጣይ ትኩረት መኾኑን ተናግረዋል። የውል እርሻ አሠራርን የማስፋት ተግባርም ሌላኛው የቀጣይ ሥራ መኾኑን ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሠራዊት ቀን አንድነታችን እንደማይናወጥ የምናሳይበት ነው።
Next article“የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአሸናፊነት ሥነ ልቦና የተገነባ ነው” ሌተናል ጀኔራል ሹማ አብደታ