
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ከተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ለማድረግ ናሙና መውሰድ ጀምሯል፡፡
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ከቀን ቀን መጨመር ስጋት ፈጥሯል፡፡ የሚያዙ ሰዎች ደግሞ እንደቀደመው ሁሉ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው ወይም ቫይረሱ እንዳለባቸው አስቀድሞ በሕክምና ተቋማት ከታወቁ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው አለመሆን ስጋቱን የበለጠ ከፍ አድርጎታል፡፡
በባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የኮሮናቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይረዳ ዘንድ ከተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናሙና እየተወሰደ ነው፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ዛሬ ሰኔ 07 ቀን 2012ዓ.ም የታክሲ አሽከርካሪዎችንና ረዳቶችን ናሙና ውሰዷል፡፡ ያነጋገርናቸው የታክሲ ረዳችና ሾፌሮችም ‘‘ማኅበረሰቡ ሳኒታይዘር ከመጠቀም ውጭ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አይጠቀምም’’ ብለዋል፡፡ የሾፌሮችና ረዳቶች ብቻ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል መጠቀም በቂ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ጭንብል መጠቀም ግዴታ ሆኖ መተግበር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
የባሕር ዳር ታክሲ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ንጉሤ ተፈራ የታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶች በየቀኑ ከበርካታ ሰዎች ጋር እንደመገናኜታቸው ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህን ተጋላጭነት ለመቀነስም ‘‘ጭንብል እንዲያደርጉ፣ ንጽሕናቸውን እንዲጠብቁና መኪናቸውን እንዲያጸዱ እያደርግን ነው’’ ብለዋል፡፡ ማኅበሩም ከጤና መምሪው ጋር በመሆን ናሙና እንዲወስዱ እያደረገ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አስማማው ሞገስ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ናሙና መውስድ ከተጀመረ አምስተኛ ቀን ማስቆጠሩን ተናግረዋል፡፡ የኮሮናቫይረስ በአገሪቱ ከተከሰተበት ገዜ ጀምሮ በከተማ አስተዳደሩ አራት ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኜባቸው የተናገሩት ኃላፊው ‘‘ናሙና የመውሰድ አቅማችን ዝቅተኛ ስለሆነ እንጂ ከዚህ በላይ ሊኖር ይችላል የሚል ግምት ስላለ ናሙና የመውሰድ ሥራ ጀምረናል’’ ብለዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እንደለዬም ተናግረዋል፡፡ ተጋላጭ ከሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል የታክሲ ረዳቶችና ሾፌሮች፣ የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ የመነኸሪያ ትኬት ቆራጮችና ተራ አስከባሪዎች፣ የሕግ ታራሚዎችና ፈታሾች፣ የጤና ተቋማትና ሌሎችም ሰዎች በጋራ የሚኖሩባቸው ካምፖች ይገኙበታል፡፡
መምሪያው 25 የናሙና መውሰጃ ቦታዎችን እንደለዬም ተናግረዋል፡፡ ናሙናውን እንዲወስዱ የክልሉ ጤና ቢሮ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ እስከ ዛሬ ሰኔ 07/2012ዓ.ም ድረስም 625 ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናሙና ተወስዷል፤ በምርመራ ውጤታቸው ከደረሱት ቫይረሱ የተገኜበት አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡
‘‘በከተማው ነዋሪ ከፍተኛ የሆነ መዘናጋት አለ’’ ያሉት መምሪያ ኃላፊው ‘‘ጥንቃቄ ማድረግ ካልቻልን በሌሎች አገሮች የምናዬው ችግር የማይመጣበት ምክንያት የለም’’ ብለዋል፡፡ መምሪያው የማኅበረሰቡ ግንዛ ከፍ እንዲል በሚችለው ሁሉ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ኅብረተሰቡ የጤና ባለሙያዎችን ምክር መስማት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ኮማንድ ፖስቱም እየተከታተለ አዋጁን ማስከበር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
ናሙና የመውሰድ ሥራው ቫይረሱ ቆመ እስኪባል ድረስ እንደሚቀጥልም ታውቋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡