
ባሕርዳር: ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ከብልጽግና ፓርቲ ሥራ አሥፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመኾን የተጠናቀቀውን የሳር ቤት ጀርመን አደባባይ ጋርመንት እና ፉሪ አካባቢ የኮሪደር ልማት ሥራ ጎብኝተናል ብለዋል።
589 ሄክታር በላይ የሚሸፍነው ከባቢ ከካዛንቺስ ቀጥሎ ሰፊው የልማት ሥፍራ ኾኗል። ፕሮጀክቱ 16 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፣ የ3 ኪሎ ሜትር ተጨማሪ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ብሎም 33 ኪሎ ሜትር የተዘረጋ የእግረኛ መንገድ አካትቷል።
የፕላዛዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ የሕፃናት መጫወቻዎች እና 5 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራ ተከናውኗል። የመኪና ማቆሚያዎች፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ኃይል መሙያ ሥፍራዎች፣ በግል እና የመንግሥት ተቋማት የተገቡ 1 ሺህ 107 ሱቆች በልማት ሥራው የተሠሩ ናቸው።
የኮሪደር ልማቱ 50 ነጥብ 5 ሄክታር አረንጓዴ ሥፍራ፣ የሕዝብ መጸዳጃዎች፣ 13 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መጋለቢያ መንገድ፣ 38 የአውቶቡስ እና ታክሲ መጫኛ ማውረጃዎችን አካትቷል ነው ያሉት። እንደዚህ ያሉት ሀገራዊ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ሥራዎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ከማሳደግ ባሻገር የትራፊክ እንቅስቃሴን በማሻሻል፣ ማኅበራዊ መስተጋብርን በማጠንከር ደማቅ ለእንቅስቃሴ ምቹ እና ዘላቂነት ያላቸው የከተማ ሥፍራዎች በመፍጠር ረገድ ዐቢይ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
