
ፍኖተ ሰላም: ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በመከናወኑ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እየቀነሱ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
በዞኑ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች አደረጃጀቶችን በማጠናከር ኅብረተሰቡ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን እየተከላከለ ነው።
በምሽት አካባቢያቸውን ተደራጅተው ሲጠብቁ ያገኘናቸው እና አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች የጸጥታ ችግሩ ካጋጠመ በኋላ በርካታ ወንጀሎች በመፈጸማቸው ወጥተው ለመግባት ተቸግረው እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ በአካባቢያቸው ተደራጅተው የሥርቆት እና ሌሎች ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ በንቃት እየጠበቁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ በሁሉም ቀበሌዎች ላይ ኅብረተሰቡን በማደራጀት አካባቢውን ከወንጀል ለመከላከል እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር መካሻው ታመነ ናቸው።
“ወንጀል ጠል ኅብረተሰብ በመፍጠር ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመኾን አሁን ላይ ይፈጸሙ የነበሩ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ማስቆም መቻሉን” አንስተዋል። በተደረገው የተቀናጀ ሥራ በከተማ አሥተዳደሩ ኅብረተሰቡ ተረጋግቶ ሥራውን እንዲያከናውን በማድረግ አንጻራዊ ሰላም ማስፈን ተችሏል ነው ያሉት።
በዞኑ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች አደረጃጀቶችን በመፍጠር “ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ተግባራት እየተከናወኑ መኾናቸውን የምዕራብ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ክፍል ኀላፊ እና ምክትል መምሪያ ኀላፊ ምክትል ኮማንደር አዳምጣቸው ዓለሙ ገልጸዋል።
በዚህም ከዚህ በፊት ይፈጸሙ የነበሩ ሕገ ወጥ ድርጊቶች እየቀነሱ መኾናቸውን አስረድተዋል።
ኅብረተሰቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ የማጠናከር እና በሌሎች አካባቢዎች የብሎክ አደረጃጀቶችን በማስፋት በሰላም ወጥቶ እንዲገባ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
