“ጣናን ተንተርሳ ለከተመችው ውቧ ከተማ የጣና ፎረም እንደ መልካም ገፀ በረከት ይቆጠራል” አምባሳደር ነብያት ጌታቸው

3

ባሕር ዳር:ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከጥቅምት 14/2018 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም የሚካሄደው የጣና ፎረም ጉባኤ በባሕር ዳር ተጀምሯል፡፡ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ጣና ፎረም “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” መርሕ ተግባራዊነት አዎንታዊ ሚና እየተወጣ መኾኑ ተነስቷል፡፡

“አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት ውስጥ” በሚል መሪ መልዕክት ለሦሥት ቀናት የሚዘልቀው ፎረም በባሕር ዳር ዛሬ ጠዋት ላይ ተጀምሯል፡፡

ፎረሙ በአዲስ አበባ እና በባሕር ዳር ለተከታታይ ቀናት ሲቀጥል በአፍሪካ የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ እየመከረ ነው።

የመክፈቻ እና የመጀመሪያውን ቀን መርሐ ግብር የምታስተናግደው ባሕር ዳር ለፎረሙ ስኬታማነት በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርጋ መጠበቋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

ከትናንት ጀምሮ የፎረሙ ተሳታፊዎች ወደ ባሕር ዳር ሲገቡ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸውም ጠቁመዋል፡፡ ይህም የከተማዋን ገጽታ በበጎ ከመገንባቱ ባሻገር አፍሪካዊ ወንድም እህቶቻችን መልካም ቆይታ እንዲኖራቸው አድርጓል ነው ያሉት፡፡

“ጣናን ተንተርሳ ለከተመችው ውቧ ከተማ የጣና ፎረም እንደ መልካም ገፀ በረከት ተደርጎ ይወሰዳል” ያሉት ቃል አቀባዩ የከተማዋን እና የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በመደገፍ በኩልም ሚናው የጎላ ሊኾን እንደሚችልም አንስተዋል፡፡

ከተማዋ ሰላም፤ ሕዝቡም እንግዳ ተቀባይ መኾኑን ያዩት እንግዶች የከተማዋን መልካም ገፅታ በመገንባት በኩል ሚናቸው የጎላ ይኾናል ነው ያሉት፡፡

ቃል አቀባዩ እንዳሉት ፎረሙ የአፍሪካ ሀገሮች መሪዎች እና ባለድርሻ አካላት በአፍሪካ የሰላም እና የደኅንነት ችግሮች ዙሪያ ተወያይተው አፍሪካዊ የመፍትሄ ሃሳቦችን ያጋራሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

ዓለም በርካታ ለውጦችን እያስተናገደች ነው ያሉት አምባሳደር ነብያት አፍሪካ በምን መልኩ ዕድሎችን ትጠቀማለች፤ እንዴትስ አቋሟን እና ቁመናዋን ታስተካክላለች የሚለው ርዕሰ ጉዳይ የፎረሙ ማጠንጠኛ ይኾናል ብለዋል፡፡

ቃል አቀባዩ ጣና ፎረም ለሌሎች አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች መነሻ ምሳሌ እየኾነ መምጣቱንም በበጎ ጎኑ አንስተዋል፡፡ አጀንዳ በመቅረጽ፣ አህጉራዊ የመፍትሄ ሃሳቦችን በማቅረብ እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ፎረሙ ጥሩ ልምዶችን እያዳበረ መምጣቱንም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጡት ካንሰር እና አሳሳቢነቱ።