የጡት ካንሰር እና አሳሳቢነቱ።

16

ባሕር ዳር: ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር በሽታዎች መካከል 30 በመቶ የሚኾነውን የሚሸፍነው የጡት ካንሰር በሽታ ነው፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል የካንሰር ሕክምና ስፔሻሊስቱ ዶክተር አማረ የሺጥላ እንደሚሉት የጡት ካንሰር በሽታ በሁለት አጋላጭ መንገዶች ሊከሰት ይችላል።

ከመጠን በላይ ውፍረት እና የሰውነት ክብደት መጨመር፣ እንቅስቃሴ የሌለው የኑሮ ዘይቤን መከተል ፣ ያልተስተካከለ የአመጋገብ ሥርዓት፣ አልኮል መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ እና መሰል ድርጊቶች ለጡት ካንሰር ሊያጋልጡ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል ብለዋል።

ሌላው ደግሞ ከሰው ልጆች ቁጥጥር ውጭ በኾነ መንገድ የሚፈጠር ሲኾን በጾታ ሴት መኾን፣ የዕድሜ መጨመር፣ የቅርብ ቤተሰብ በጡት ካንሰር በሽታ መያዝ እና የመሳሰሉት ተፈጥሯዊ ምክንያቶች መኾናቸውን ጠቅሰዋል።

ጡት ላይ ሕመም የሌለው እብጠት መኖር፣ የጡት ጫፎች ወደ ውስጥ መሰርጎድ (መግባት)፣ የቆዳ ቀለም ላይ ለውጥ መምጣት፣ ጊዜው እየረዘመ በሄደ ቁጥር ደግሞ መቁሰል እና በጡት ጫፍ ፈሳሽ መውጣት ደረጃው ከፍ እያለ በሄደ ቁጥር እብጠት ማስከተል የጡት ካንሰር ምልክቶች ሊኾኑ እንደሚችልም ተናግረዋል።

እነዚህ ምልክቶች ባይታዩም እንኳን የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ይህም በሽታው ከተከሰተ አፋጣኝ መፍትሔ ለመፈለግ ካልተከሰተም አስቀድሞ ለመከላከል ዕድል ይሰጣል ነው ያሉት።

አሁን ላይ የጡት ካንሰር በሽታ በኢትዮጵያ አሳሳቢ በሚባል ደረጃ እየተስፋፋ መኾኑን ያነሱት ዶክተር አማረ በሽታው ቢከሰትም እንኳን በየደረጃው ሕክምና እንደሚሰጥ ነው የገለጹት፡፡

የጡት ካንሰር በሽታ ብዙም ያልተሰራጨ ከኾነ ቀዶ ሕክምና ማድረግ የሚቻል ሲኾን በደም ስር የሚሰጥ የኬሞ ቴራፒ ሕክምና፣ የሆርሞን ሕክምና እንዲሁ የጡት ካንሰር ከተከሰተ በኋላ በየደረጃው የሚሰጡ የሕክምና አገልግሎቶች ተጠቃሽ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡

የጡት ካንሰር የአሳሳቢነቱን ያህል ትኩረት ሳይሰጠው ዘመናት አልፈዋል፡፡ አሁን ላይ ግን በመንግሥት ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት በንቅናቄ እየተሠራበት መኾኑን አንስተዋል።

በገጠር የሚኖሩ ወገኖችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግም አዋጭ ስልቶችን መርጦ ዘላቂነት ያለው ሥራ ማከናወን እንደሚገባ የካንሰር ሕክምና ስፔሻሊስቱ ዶክተር አማረ አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት እና ዓለመቀፍ የሥራ ድርጅት(ILO) የሥራ ስምሪት እና ፍልሰትን አስመልከቶ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ።
Next article“ጣናን ተንተርሳ ለከተመችው ውቧ ከተማ የጣና ፎረም እንደ መልካም ገፀ በረከት ይቆጠራል” አምባሳደር ነብያት ጌታቸው