
አዲስ አበባ:ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ዴሞክራሲያዊ ልማት ይፋጠን ዘንድ በሳይንሳዊ ዘዴ የተሠበሠቡ እና የተተነተኑ ስታቲስቲካዊ መረጃዎች መሠረታዊ ናቸው።
ለዚህ ይረዳ ዘንድ የዓለም የሥራ ድርጅት ለኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ለሥራ ጥራት አስፈላጊ የኾኑ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከናሙና ዳሰሳዎች፣ ቆጠራዎች እና አሥተዳደራዊ መዝገቦች መረጃ ለመሠብሠብ፣ ለማዘጋጀት እና ለተለያዩ ዘርፎች እና ተጠቃሚዎች የተተነተኑ ሪፖርቶችን በማቅረብ ማዕከላዊ ሚና የሚጫዎት መንግሥታዊ ተቋም ነው።
ተቋሙ ከዓለም የሥራ ድርጅት(ILO) የሥራ ስምሪት እና ፍልሰትን አስመልከቶ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ፈርሟል። ለሥራ ቅልጥፍና እና ጥራት የሚኾኑ ቁሳቁሶችንም ከዓለማቀፍ የሥራ ድርጅት ድጋፍ ተደርጎለታል።
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ የተገኙት የአገልግሎቱ ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር በከር ሻሌ አገልግሎቱ የኢትዮጵያን መንግሥት የመረጃ ፍላጎት መሠረት አድርጎ እንደሚሠራ ገልጸዋል። የዓለም የሥራ ድርጅትም አንዱ የመረጃ ተጠቃሚ በመኾኑ በትብብር እየሠሩ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
የዓለም የሥራ ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር ኩምቡላ ንዳባ በማንኛውም ሀገር ፖሊሲ ለመቅረጽ እና ውሳኔ ለመስጠት የስታቲስቲክስ መረጃ አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል።
የመረጃዎች ጥራት አለመኖር የወቅቱ ፈተና እንደኾነም ጠቁመዋል። ይህን ችግር ለመፍታት ትግል ላይ መኾናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ የተደረገው ድጋፍም ይሄን ታሳቢ ያደረገ እንደኾነ ነው ያብራሩት።
በዓለም የሥራ ድርጅት ውስጥ ቺፍ ቴክኒካል አድቫይዘር አይዳ አዎል (ዶ.ር) የዓለም የሥራ ድርጅት ከሚሠራቸው ሥራዎች ውስጥ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እና ፍልሰትን የተመለከቱ እንደኾኑ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎትም መረጃ የመስጠት ተግባሩን እንዲወጣም ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
የዓለም የሥራ ድርጅት ለአገልግሎቱ የመሠብሠቢያ ጠረጴዛ፣ ላፕቶፕ፣ ወንበር እና ኤልጅ ስክሪን ድጋፍ ያደረገ ሲኾን ከአሁን በፊትም ለሠራተኞቹ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንደሰጠም ተገልጿል።
በቀጣይም በተቋማቱ ጥራት ያለው እና የተደራጀ የስታቲስቲክስ መረጃ ፍሰት እንዲኖር በጋራ እንደሚሠሩም አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ በለጠ ታረቀኝ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
