የጤናው ዘርፍ ስኬታማነት በታከሙ ታካሚዎች ብዛት ብቻ ሳይኾን እንዳይታመሙ በሚሠሩ አዳዲስ የጤና ሥራዎችም ነው የሚለካው።

7

አዲስ አበባ:ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጅማ ከተማ “ዘላቂ ኢንቨስትመንት እና ኢኖቬሽን ለጠንካራ የጤና ሥርዓት” በሚል መሪ መልዕክት 27ኛው የጤና ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።

ዜጎች አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጤናቸው ተጠብቆ አምራች ዜጋ እንዲኾኑ ለማድረግ የጤና ሥርዓቱ ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታት ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ እንዳለ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ ለሕዝቡ ጤና መሻሻል ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ አዳዲስ መፍትሄዎችን እና ኢኖቬሽኖችን ማምጣት አስፈላጊ መኾኑን ጠቅሰዋል።

ዘላቂ ኢንቨስትመንት እና ኢኖቬሽን ጠንካራ የማይበገር ፍትሐዊ እና ራስን የመቻል የጤና ሥርዓት ጉዞን የሚያፋጥን እንደኾነ አመላክተዋል።

ባለፉት ጊዜያት ተላላፊ በሽታዎችን በመከላከል የእናቶች እና የሕጻናትን ጤና ማሻሻል እንደተቻለም አስገንዝበዋል።

የጤና መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት በተላላፊ በሽታዎች የሚደርሱ ሞት እና ጉዳትን መቀነስ እንደተቻለም ጠቁመዋል።

እነዚህ ስኬቶችም በሕዝቡ እና በጤናው ዘርፍ ባሉ ሠራተኞች እና መሪዎች ቁርጠኛ ሥራ የመጡ እንደኾነም ዶክተር መቅደስ ዳባ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በግሉ ሴክተር የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ እንደኾነ ያብራሩት ሚኒስትሯ በቀጣይም ጤናን እንደስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት በመመልከት በጤናው ዘርፍ ከፋርማሲዩቲካል ማምረቻ እስከ ጤና ተቋማት ግንባታ ድረስ በሰፊው እንዲሳተፉ ዕድሎች ተመቻችተዋል ብለዋል።

በጤናው ዘርፍ ዲጂታል የጤና መፍትሄዎችን ለማሳደግ እና ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ እንዳለም አብራርተዋል።

ዶክተር መቅደስ ዳባ “ስኬታማነታችን በተገነቡት ተቋማት ብዛት፣ በሠራናቸው ሥራዎች እና በታከሙት ታካሚዎች ብዛት ሳይኾን በመጀመሪያ ደረጃ እንዳይታመሙ በሚሠሩ አዳዲስ ሥራዎች የሚለካ ነው” ብለዋል።

የማኅበረሰብ ተሳትፎን ማላቅ፣ የፋይናንስ ሥርዓቱን ማሳለጥ እና የጤና አገልግሎት ሥረዓቱን ከፍ ማድረግ የበጀት ዓመቱ ዋና ትኩረት እንደኾነም አብራርተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የኢኖቬሽን አቅምን በማሳደግ ፍትሐዊ የሕክምና አገልግሎትን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ የአገልግሎት እርካታ የሚገኝበትን ጠንካራ ሥራ በጋራ መገንባት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በ27ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባኤ ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል መሪዎች ተገኝተዋል።

በዚህ መድረክ ላይም በጤናው ዘርፍ የተሻለ ምርምር የሠሩ፣ ለኅብረተሰቡ ውጤታማ የጤና አገልግሎት የሰጡ፣ ረጅም ዘመን በክብር ያገለገሉ እና ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሥራቸውን የፈፀሙ የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎች ዕውቅና እና ሽልማት እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን አሰፌ -ከጅማ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጤናው ዘርፍ ስኬታማነት በታከሙ ታካሚዎች ብዛት ብቻ ሳይኾን እንዳይታመሙ በሚሠሩ አዳዲስ የጤና ሥራዎችም ነው የሚለካው።
Next article“ነጻ ሃሳብ፣ ግልጽ ውይይት እና አሕጉራዊ የመፍትሔ አቅጣጫ የጣና ፎረም መለያዎች ናቸው” አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው