
ባሕር ዳር:ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ መቅደስ አናብል በባሕር ዳር ከተማ የሚኖሩ የሦሥት ልጆች እናት ናቸው።
ወይዘሮ መቅደስ ለአሚኮ እንደተናገሩት ልጆቻቸው ላይ በተደጋጋሚ የራስ ቅላቸው ላይ የሚወጣ የሚያሳክክ ቁስል የልጆቹን ፀጉር ለመላጨት እንዳስገደዳቸው ገልጸዋል።
ቁስለቱ ከየት መጣ ሳይባል በፍጥነት እንደሚራባ እና በቁስለቱም ላይ መጥፎ ሽታ ያለዉ ፈሳሽ ልጆቹን ያስቸግራቸው እንደነበር ለአሚኮ ገልጸዋል።
በተደጋጋሚ የልጆች የራስ ቅል ላይ የሚቀባ ባሕላዊ መድኃኒት መጠቀማቸውን እና ያም ቢኾን ምንም ለውጥ አለማምጣቱን ተናግረዋል።
የራስ ቆዳ ፈንገስ በሕክምናው እንዴት እንደሚታይ አሚኮ ያናገራቸው የባሕርዳር ፈለገ ሕይወት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕጻናት ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር አያል መኳንንት ፈንገሱ ቲኒያ ካፒቲስ በተባለ የፈንገስ ኢንፌክሽን የሚፈጠር ነው ብለዋል።
ቲኒያ ካፒቲስ የራስ ቅል ፈንገስ በሕጻናት ላይ በብዛት የሚታይ ሲኾን የፀጉር ሥሮችን እና የራስ ቅልን ያጠቃል። ይህ ኢንፌክሽን ለፀጉር መርገፍ፣ ለቆዳ መላጥ እና ለሕመም ሊዳርግ እንደሚችልም ዶክተር አያል መኳንንት ገልጸዋል።
“የራስ ቆዳ ፈንገስ” ወይም “የራስ ቅል ላይ የሚወጣ እከክ” በሚል የሚጠራው ቲኒያ ካፒቲስ የሚከሰተው በቆዳ ላይ በሚኖሩ ጥቃቅን ፈንገሶች (dermatophytes) ነው።
እንደ ዶክተር አያል መኳንንት ገለጻ እነዚህ ፈንገሶች በዋነኝነት የሚተላለፈውም በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ቀጥታ በመነካካት፣ በጋራ ዕቃዎች በመጠቀም ማለትም የፀጉር ብሩሽ (ማበጠሪያ) ባርኔጣዎች፣ ኮፍያዎች፤ የትራስ ልብሶች፣ የፀጉር ማስጌጫዎች እና በቂ ጽዳት ባልተደረገላቸው የፀጉር መቁረጫ ዕቃዎች በከፍተኛ ሁኔታ ፈንገሱ እንደሚተላለፍ ገልጸዋል።
ሌላው የሚተላለፍበት መንገድ ከእንስሳት ወደ ሰው ማለትም እንደ ድመቶች፣ ውሾች፣ ጥንቸሎች እና ሌሎች የቤት እንስሳት ፈንገሱን ወደ ሰው ሊያስተላልፉ ይችላሉ። በተለይ ቡችላዎችና ድመቶች ለዚህ ተጋላጭ ናቸው ነው ያሉት።
የራስ ቆዳ ፈንገስ ምልክቶች እንደየ በሽታው ዓይነት እና የሰውየው የበሽታ የመከላከል አቅም ሊለያዩ ይችላሉ ያሉት ዶክተር አያል ሙኳንንት ቲኒያ ካፒቲስ የራስ ቅል ፈንገስ የተለያዩ ምልክቶች አሉት ብለዋል።
ከእነዚህም ምልክቶች ውስጥ
የህፃናት ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር አያል መኳንንት ይህን ህመም ማከም የሚቻለው የፀጉር ሥሮችን ዘልቀው መግባት የሚችሉ ፀረ-ፈንገስ መድኃኒቶችን በመጠቀም ነው ብለዋል።
በአፍ የሚወሰዱ ፀረ-ፈንገስ መድኃኒቶች ኢንፌክሽኑን ከውስጥ ለማጥፋት ቁልፍ መድኃኒት እንደኾኑም አስረድተዋል።
ግሪሲኦሊቪያን የተባለ መድኃኒት በብዛት ለልጆች የሚታዘዝ ሲኾን ከስድስት እስከ ስምንት ሳምንታት እና ከዚያ በላይ መወሰድ ሊያስፈልግ ይችላል ነው ያሉት።
ይህ መድኃኒት ምግብ በደንብ በልቶ መውሰድ የሕክምናውን ውጤታማነት ይጨምራል ሲሉም ገልጸዋል።
በተጨማሪም በሽታውን ለማከም በሐኪም ትእዛዝ የሚሰጡ ሌሎች አማራጮች እንዳሉም የሕጻናት ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር አያል መኳንንት አብራርተዋል።
በሽታው የሕክምና ባለሙያ ክትትል የሚፈልግ በመኾኑ ማንኝውም ወላጅ ልጆቹ ላይ ምልክቶች ሲጀምሩ ወዲያውኑ ማሳከም እና የተሰጡትን የመድኃኒት መመሪያዎች በትክክል መከተል በጣም አስፈላጊ እንደኾነ ነው ያስገነዘቡት።
ሕክምናውን በአግባቡ ካልተከታተሉ በሽታው ሊባባስ እና ዘላቂ የፀጉር መርገፍ ሊያስከትል እንደሚችልም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
