
እንጅባራ: ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ622 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ አስታውቋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በተያዘው በጀት ዓመት ከመደበኛ ገቢ እና ከአገልግሎት ገቢ ከ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል።
በመጀመሪያው ሩብ ዓመትም በዓመቱ ከታቀደው ገቢ ውስጥ ከ622 ሚሊዮን ብር በላይ የሚኾነው መሰብሰቡን የተናገሩት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ፈጠነ ጥላሁን ናቸው።
የተሰበሰበው ገቢ በሩብ ዓመቱ ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ 88 በመቶ ነው። ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 83 ከመቶ በላይ ብልጫ የታየበት ነው ብለዋል።
የሰላም ሁኔታው እየተሻሻለ መምጣቱ፣ የኅብረተሰቡ ግብር የመክፈል ባሕል ማደጉ፣ ግብር በሚሰውሩ አካላት ላይ እየተወሰደ ያለው አስተማሪ እርምት እና የገቢ አዋጆች መሻሻላቸው ለገቢ ማደጉ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም አንስተዋል።
ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት እስከ በጀት ዓመቱ መገባደጃ ድረስ የታቀደውን ገቢ አሟጠው ለመሰብሰብ በቁርጠኝነት እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
“የሚታቀዱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ዳር የሚደርሱት በሚሰበሰበው ገቢ ልክ ነው” ያሉት ኀላፊው ግብር ከፋዮች የተወሰነላቸውን ግብር በወቅቱ እና በታማኝነት መክፈል እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
