
ደሴ:ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የ2018 የተማሪዎች የምገባ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል።
በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር በ2015 ዓ.ም በሁለት ትምህርት ቤቶች የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ አሁን ላይ በ20 ትምህርት ቤቶች እየተካሄደ ይገኛል።
ምገባው ከተጀመረ ጀምሮ በተማሪዎች ላይ ከአካላዊ ለውጥ ባሻገር በትምህርታቸው ውጤት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ችሏል ተብሏል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መንግሥቱ አበበ የተማሪዎች ምገባን በ5ሺህ ተማሪዎች በመጀመር በ2017 ዓ.ም 12ሺህ ተማሪዎች ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት።
በዚህ ዓመት ከ15ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመመገብ ከ97 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ከዚህም ውስጥ 40 በመቶው በማኅበረሰብ ተሳትፎ እንደሚሸፈን ገልጸዋል።
በ2017 ዓ.ም ማኅበረሰቡ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ለተማሪዎች ምገባ አሰተዋጽኦ ማድረጉንም አንስተዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሐመድ አሚን የሱፍ ትልቁ ኢንቨስትመንት ልጆች ላይ የሚደረገው ነው ብለዋል።
የነገን ኢትዮጵያ መረከብ የሚችል ትውልድ መገንባት የሚቻለው ትምህርት ቤት ላይ ሢሠራ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
የተማሪዎች ምገባ ተቋማዊ ቅርጽ እንዲይዝ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ከንቲባው ማኅበረሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ አበሻ አንለይ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!