
ባሕር ዳር: ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ባወጣው የ2025 ዓለም አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ትንበያ መሠረት በዓለም ዙሪያ የሳይበር ወንጀል በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው። ሰው ሠራሽ አስተውሎት ደግሞ ለዚህ ሥጋት መጨመር እንደ ምክንያት እና እንደ መከላከያ ተደርጎ ተመላክቷል።
የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ሲኾን ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በአንድ ተቋም ላይ የሚሰነዘረው አማካይ ሳምንታዊ የሳይበር ጥቃት ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሯል ይላል መረጃው።
እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2021 ዓ.ም ሁለተኛ ሩብ ዓመት በቁጥር 818 የነበረው ሳምንታዊ የሳይበር ጥቃት በ2025 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ወደ 1 ሺህ 984 ማሻቀቡን ትንበያው ጠቁሟል።
ከዚህ ሥጋት ጋር ተያይዞ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ባለሁለት ስል ኾኖ ሁለት የሚገፋፉ ሚናዎችን እየተጫወተ ይገኛል።
የሳይበር ወንጀለኞች ትዕዛዝን በጽሑፍ በመቀበል የሚሠሩ ጄኔሬቲቭ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎችን እና ድረ ገጾችን በመጠቀም አታላይ ማስፈንጠሪያዎችን (phishing) እየላኩ የማንነት መረጃዎችን እያፈተለኩ እና ለቀጣይ የጥቃት ተግባራቸው ምቹ ሁኔታን ይፈጥሩበታል።
ለምሳሌ የተቋማትን ከፍተኛ ሥራ አሥፈጻሚዎች ድምጽ እና ምስል በማስመሰል የፋይናንስ ሠራተኞችን ማታለል ከጥቃት ዓይነቶች ውስጥ ተመዝግቧል። ለሳይበር ደኅንነት የሚመደበው በጄት በ2022 ከነበረው 17 በመቶ ዕድገት በ2025 ቀንሶ ወደ 4 በመቶ ዝቅ ብሏል።
የባለሙያዎች እጥረትም ሌላኛው ችግር ነው፡፡ ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው በዓለም አቀፍ ደረጃ 14 በመቶ የሚኾኑ ድርጅቶች ብቻ ለሥራቸው ተስማሚ የኾነ የሳይበር ደህንነት ባለሙያ አላቸው። የባለሙያዎች እጥረት ባለበት ኹኔታ በርካታ ተቋማት ጥቃቶችን ለመመከት ወደ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ እየዞሩ መኾኑንም ፎረሙ ያወጣው ጽሑፍ ያትታል።
ጽሑፉ ወንጀለኞች የማኅበራዊ ምሕንድስና (Social Engineering) ዘዴዎች በመጠቀም የተቋማት ሠራተኞች እንደኾኑ በማስመሰል (Impersonation) ወደ ዲጂታል ሥርዓቶቻቸው ዘልቀው በመግባት ጥቃትን መፈጸም የተለመደ እየኾነ መምጣቱን ገልጾ የሳይበር ደህንነት ቴክኒካዊ ክህሎት ሳይኾን የሕይወት ክህሎትነቱ እየጎላ መምጣቱን ይጠቁማል።
የሳይበር ወንጀል ድንበር አልባ በመኾኑ የዓለም አቀፍ ትብብር የሚያሻው ጉዳይ መኾኑም ተመላክቷል። ከወራት በፊት ዓለም አቀፍ የፖሊስ ትብብር እና አፍሪፖል ጋር በመተባበር በአንጎላ የሚገኙ 25 የምናባዊ ገንዘብ (ክሪፕቶከረንሲ) መፍጠሪያ ማዕከሎችን ማጥፋታቸው የድንበር ተሻጋሪ ትብብር ውጤታማነት ማሳያ ነው ሲል በሪፖርቱ አስነብቧል።
የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም መረጃ እንደሚያሳየው ተቋማት እያደገ የመጣውን የሳይበር ሥጋት ለመቋቋም የፋይናንስ እና የሰው ኃይል ክፍተቶችን በሰው ሠራሽ አስተውሎት በመሙላት የዓለም አቀፍ ትብብርን በማጠናከር እና ሠራተኞቻቸውን በማሠልጠን ሁሉን አቀፍ የጥቃት መመከቻ ስልቶችን መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል።
በዘመኑ መኮንን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!