
ባሕር ዳር: ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከልክ በላይ ደርቆ መርገፍ፣ በዝናብ መበስበስ፣ በበረዶ መርገፍ፣ በምስጥ መበላት፣ በውቂያ ጊዜ ብልሽት፣ በማጓጓዝ ጊዜ መባከን እና ሌሎችም ከምርት ብክነት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እንደ ዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) መረጃ በኢትዮጵያ የቅድመ ምርት ብክነት ከ25 እስከ 30 በመቶ ይደርሳል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አበበ ጌታቸው በ2017/18 የምርት ዘመን 563 ሺህ ሔክታር መሬት በሰብል መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡
ሰብል እየተሰበሰበ መኾኑን እና የምርት ብክነት ከ4 በመቶ እንዳይበልጥ ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ነው አቶ አበበ የገለጹት፡፡
ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ በመፍጠር የተለያዩ ስልቶችን እንዲጠቀሙ እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የተለያዩ መውቂያ ማሽኖች፣ መቋጠሪያ ከረጢቶች፣ የብረት ጎተራዎች እየተለመዱ ነውም ብለዋል፡፡
ባለፈው የምርት ዘመን 51 ማሽኖች አገልግሎት ላይ ውለዋል ብለዋል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ 191 አነስተኛ መውቂያ ቴክኖሎጂዎች መኖራቸውንም ነው የተናገሩት። ይህም ኾኖ መውቂያ ማሽን እጥረት መኖሩን ገልጸዋል፡፡
ሦስት አጭዶ የሚወቃ ማሽን ጥያቄ አቅርበን በመጠባበቅ ላይ ነን ብለውናል፡፡ በተጨማሪም የማሽን ኪራይ ለማቅረብ እየተሠራ እንደኾነም አንስተዋል፡፡
በማኅበራት በኩልም ቴክኖሎጂዎችን የማቅረብ ሥራ እንደሚሠራ አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አምሳሉ ጎባው በምርት ዘመኑ ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የቅድመ ምርት ብክነትን መከላከል የቢሮው አንድ ሥራ እንደኾነም ጠቅሰዋል፡፡ በሰብል ፓኬጅ ሥልጠና፣ በተግባር ድጋፍ፣ የማጨጃ እና መውቂያ ማሽኖችን በማቅረብም እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
ሰሊጥ በደረሰባቸው አካባቢዎች የጉልበት ሠራተኛ እንዲቀርብ በማመቻቸት እና በመረዳዳት እንዲሰበሰብ እንዲሁም ቴክኖሎጂን በመጠቀም እንዲሰበስቡ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ከኤክስቴንሽን አገልግሎት እስከ ሚዲያ መረጃ ድረስ ግንዛቤ እየተፈጠረ እና ግፊት እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
ምዕራብ ጎጃም፣ ምሥራቅ ጎጃም እና ሰሜን ሸዋ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በጉልሁ ተጠቃሽ መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡ አርሶ አደሮች በተናጥልም ኾነ በማኅበራት አማካኝነት ማሽኖችን በመጠቀም ምርት በመሰብሰብ ብክነትን የመቀነስ ልምዱ እየሰፋ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
በቀጣይም በክልሉ ሙሉ አቅምን በልማቱ ላይ በማዋል የተሻሻሉ አሠራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምርት ብክነትን የመቀነስ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት አቶ አምሳሉ፡፡
ዘጋቢ:- ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
