
ደብረ ማርቆስ፡ ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምሥራቅ ጎጃም ዞን የቡና ምርትን በስፋት እና በጥራት ለማምረት የሚያስችል ጸጋ ያለው ዞን ነው። በዞኑ ወረዳዎች የቡና ምርትን በጥራት እና በሚፈለገው ልክ በማምረት የአርሶ አደሮችንም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው።
በባሶ ሊበን፣ በማቻከል፣ በደብረ ኤሊያስ እና ጎዛምን ወረዳዎች የቡና ምርት ውጤታማ በመኾኑ በዘርፉ የተሻለ ምርት ለማምረት ትኩረት መሰጠቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኅላፊ አበበ መኮንን ለአሚኮ ገልጸዋል።
ቡና እና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞችን በማፍላት እና በማሰራጨት የአካባቢውን አርሶ አደሮች የመደገፍ ሥራ እንደሚከናወንም ነው የገለጹት። ለዚህ ተግባር ደግሞ የችግኝ ጣቢያ ማዕከላትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ የቡና ልማትን በማጠናከር ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ከዞን እስከ ወረዳዎች በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል። የዞኑን የቡና ማምረት አቅም በመጠቀም የአርሶ አደሮችን ሕይወት የሚለውጥ እና ለገበያም ተወዳዳሪ የሚያደርግ ምርት ይዞ መቅረብ ይጠበቃል ብለዋል።
ዞኑ ለቡና ምርት ተስማሚ የአየር ንብረት ያለው በመኾኑ የቡና እና ፍራፍሬ ልማትን ከሌሎች የግብርና ሥራዎች ጋር በትኩረት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
