አርሶ አደሮች ሁሉንም የውኃ አማራጮች ተጠቅመው እንዲያመርቱ እየተሠራ ነው።

5

ከሚሴ:ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደዋጨፋ ወረዳ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።

 

በጉብኝቱ የጨፋ የተቀናጀ እርሻ ልማት የወላጅ እናት ዶሮ ፕሮጀክት፣ በወረዳው እየተሠራ ያለውን የዘር ብዜት እና የሰብል ሥራ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

 

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሀሰን ሰይድ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በመኸር ሰብል ከ58 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል መሸፈኑን ገልጸዋል።

 

የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካም ተገቢው የሰብል ጥበቃ እና የተባይ አሰሳ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

 

ከመኸር ልማቱ በተጨማሪ በመስኖ ልማት ከ17 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን መታቀዱን ገልጸዋል።

 

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ በምርት ዘመኑ የአርሶአደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም በመለየት ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

 

አካባቢው ለመስኖ ልማት አመቺ መኾኑን ጠቅሰዋል። አርሶ አደሮች ሁሉንም የውኃ አማራጮች ተጠቅመው እንዲያመርቱ ለማስቻል ይሠራል ብለዋል።

 

የብሔረሰብ አሥተዳደሩን ተረጂዎች በራስ አቅም ለመርዳትም አስቻይ ሁኔታዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።

 

ከተረጅነት ለመላቀቅ እና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን ለአርሶአደሮች ለማቅረብም በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አስረድተዋል።

 

የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶአደሮችን በማደራጀት ብድር ለማመቻቸትም ታስቦ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

 

ብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሌማት ትሩፋት ዘርፍ እምቅ አቅም ያለው መኾኑን ጠቅሰዋል። በቀጣይ በትኩረት እንደሚሠራም አስገንዝበዋል።

 

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዋልያ ቁጥርን ለመጨመር እየተሠራ ነው። 
Next articleየሃይማኖት አባቶች ሰላምን ለማስፈን ሚናቸውን መወጣት አለባቸው።