
ደባርቅ: ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት የፓርኩን ልማት እና ጥበቃ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር በደባርቅ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቢምረው ካሳ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በዞኑ የሚገኙ ስድስት ወረዳዎችን የሚያዋስን እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ማኅበረሰባዊ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት እና የቱሪዝም ተደራሽነትን ለማሳደግ በቅድሚያ የፓርኩን ደኅንነት በተገቢው መንገድ መጠበቅ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በፓርኩ ላይ እየደረሱ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የዞን አሥተዳደሩ በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አስራት ክብረት ፓርኩ ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንጻር ደኅንነቱን ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ፓርኩን ከመጠበቅ ባለፈ በፓርኩ ላይ ጥቃት የሚያደርሱ አካላትን ሕጋዊ አግባብነት ያለው አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እየተከናዎነ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የፓርኩን የቱሪዝም መዳረሻነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም አንስተዋል።
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ ላቀው መልካሙ ልቅ ግጦሽ፣ ሕገ ወጥ የእንስሳት አደን እና ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ የፓርኩን ደኅንነት እየፈተኑት እንደሚገኙ ተናግረዋል። ፓርኩን ከጥፋት ለመታደግም ጽሕፈት ቤቱ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።
ከነዚህም ተግባራት መካከል የጥናት እና ምርምር ሥራዎች፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት እና ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር የአካባቢውን ማኅበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተጠቃሽ ናቸው ነው ያሉት።
ቁጥሩ እየቀነሰ የሚገኘውን ዋልያ ለመጨመር “ዋልያ ሪከቨሪ” የሚል ጥናት ተጠንቶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
የፓርኩን ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ በመኾኑ ድጋፎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ከመሥራት ጀምሮ የሚመለከታቸውን አካላት በተደጋጋሚ በማሳወቅ፤ የፓርኩ ችግር ትኩረት እንዲያገኝ የማድረግ ተግባር ማከናወናቸውን ነው የገለጹት።
የሰሜን ጎንደር ዞን የሀገር ሽማግሌዎች ማኅበር ሰብሳቢ መጋቤ ሰላም አየልኝ ክብረት ፓርኩን ከጥፋት ለመጠበቅ በሚደረጉ ጥረቶች በመሳተፍ እና ፈጣን ምላሽ በመስጠት ጥረት ሲያደርጉ መቆያታቸውን ገልጸዋል።
ሌላው ተሳታፊ በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የቀይ ቀበሮ ምግብ አብሳይ ማኅበር ሰብሳቢ አድኖ አቡሃይ በሥራቸው የሚገኙ 65 አባላትን በአካባቢው በማሰማራት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ተሳታፊዎቹ በዘላቂነት ፓርኩን ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካል ተሳትፎ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!