በምርት ዘመኑ ለመስኖ ልማት ትኩረት በመስጠት እየተሠራ ነው። 

2

ከሚሴ:ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደዋጨፋ ወረዳ የግብርና ልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

 

በጉብኝቱ የጨፋ የተቀናጀ እርሻ ልማት የወላጅ እናት ዶሮ ፕሮጀክት፣ በወረዳው እየተሠራ ያለው የዘር ብዜት እና የሰብል ሥራውን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

 

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከተረጅነት በመላቀቅ ራስን ለመቻል አስቻይ አቅም ያለው መኾኑን ማረጋገጥ እንደቻሉ ተናግረዋል።

 

የጨፋ የተቀናጀ እርሻ ልማት የወላጅ እናት ዶሮ ፕሮጀክት ከ10 ሺህ በላይ ዶሮዎችን በማስገባት የጀመረው ሥራ አበረታች መኾኑን ጠቅሰዋል። በቀጣይ የቀጣናውን የስጋ ዶሮ እና የእንቁላል ፍላጎት ማሟላት የሚችል ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

 

በሰብል ልማት ዘርፍ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን በማባዛት ለአርሶአደሮች እያቀረበ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

 

ይህም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የላቀ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

 

በምርት ዘመኑ ለመስኖ ልማት ትኩረት በመስጠት እየተሠራ እንደኾነም አብራርተዋል። አንድ አርሶአደር ቢያንስ አንድ የውኃ አማራጭ እንዲኖረው ለማድረግ ታስቦ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል።

 

በምርት ዘመኑ የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካም ከዚህ በፊት የተገነቡ የመስኖ አውታሮችን በመጠገን እና የከርሰ ምድር እና የገፀ ምድር ውኃን በሙሉ አቅም ለመጠቀም እንደሚሠራም አሥረድተዋል።

 

በክልሉ ከ5 ሺህ በላይ የውኃ መሳቢያ ሞተሮች መቅረባቸውን ጠቅሰዋል። ለአርሶአደሮች የማሰራጨት ሥራ እየተሠራ እንደኾነም አንስተዋል።

 

መስኖ በዚህ ዓመት ትልቅ የአስተሳሰብ ለውጥ የሚመጣበት የሥራ ዘርፍ ኾኖ እንዲመዘገብ ለማድረግም ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መኾኑንም አስገንዝበዋል።

 

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፍትሕ ሪፎርሞች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ነው።
Next articleየዋልያ ቁጥርን ለመጨመር እየተሠራ ነው።