
ገንዳ ውኃ: ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዳኞች እና የፍትሕ አካላት የ2017 ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክን በገንዳ ውኃ ከተማ አካሂደዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዳኞች አሥተዳደር ንዑስ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አራጋው መንግሥቱ ወንጀለኛን አቅርቦ የፍርድ ውሳኔ በወቅቱ ለመስጠት የጸጥታ ችግሩ በፍርድ ቤቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።
ይህም የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓቱን ወደ ኋላ አስቀርቶታል ነው ያሉት።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮማንደር ምስጋናው ካሴ በአካባቢው የሚስተዋሉ ወንጀሎችን፣ እገታ እና ዝርፊያን ለመከላከል እና ለማስቆም በየደረጃው ካለው የጸጥታ መዋቅር ጋር በቅንጅ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
አካባቢው ጠረፍ በመኾኑ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውሮች የሚስተዋሉበት በመኾኑ በቀጣይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራበትም ኮማንደሩ አስገንዝበዋል።
ሁለንተናዊ ሰላምን ለማምጣት የጸጥታ መዋቅሩ ከፍትሕ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ፍትሕ መምሪያ ኀላፊ ቢታው አሳዬ የሰላም እጦቱ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል። በዞኑ “አስተማማኝ ሰላምን ለማምጣት የፍትሕ ተቋማት በርትተው ሊሠሩ ይገባል” ብለዋል።
የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተጨባጭ የዳኝነት እና የፍትሕ ትብብር ሥራው ሊጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
“የፍትሕ ሪፎርሞች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መኾኑንም” ተናግረዋል። ውስንነቶችን በማረም ቀጣይ የተሻለ ሥራ ይሠራል ነው ያሉት።
የፍትሕ ሥራዓቱን በማዘመን ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እንደሚሠራም ኀላፊው አብራርተዋል።
እንደ ዞን የፍትሕ ሥራዓቱን ለማዘመን ተቋማት የኢ-ፋይሊግ ቴክኖሎጅን እንዲጠቀሙ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
የክልሉን የአሻጋሪ ልማት ዕቅድ እውን ለማድረግ የፍትሕ ተቋማት በልዩ ትኩረት ከላይኛው እስከ ታችኛው ድረስ እየሠሩ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ኢብራሒም የሱፍ ማኅበረሰቡ ለሕግ እና ለፍትሕ ሥራዓቱ ተባባሪ በመኾን ጥፋተኞችን በማጋለጥ የፍትሕ ሥራዓቱን ማጠናከር እንዳለበትም ተናግረዋል።
በጸጥታው ምክንያት ውሳኔ ሳያገኙ በማረሚያ ቤት ያሉ ታራሚዎች ትክክለኛ ፍርድ እንዲያገኙም በተገቢው መንገድ ይሠራል ነው ያሉት።
በፍትሕ ተቋማት ላይ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ በተቋማቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማረም ጥረት መደረጉንም ፕሬዝዳንቱ አንስተዋል።
በቀጣይ የተሻላ የዳኝነት ሥርዓት በመዘርጋት አገልግሎቱን ፈጣን እና ቶሎ ፍርድ ሰጭነትን እውን በማድረግ ማኅበረሰቡን ማርካት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!