
ባሕር ዳር: ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባየር ላይፍ ሳይንስ ኢትዮጵያ የተሰኘ ድርጅት ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በመስኖ የሚለማ የበቆሎ ዝርያ አስተዋውቋል።
ዲኬ 777 በተባለው የበቆሎ ዝርያ ትውውቅ የምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ጎጃም፣ አዊ እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች የግብርና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
የትውውቅ ውይይቱን የከፈቱት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው የበቆሎ ምርት በአማራ ክልል ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዝ ገልጸዋል።
ምርት እና ምርታማነቱን ለማሳደግም የተሻሻለ ዝርያ የመጠቀምን አስፈላጊነት ጠቅሰዋል።
ውይይቱም ዝርያውን በክልሉ ለማስፋት መኾኑን ገልጸዋል። በቆሎው ምርታማ እና ለክልሉ ሥነ ምህዳር ተስማሚ በመኾኑ በዞኖች እየተሞከረ ነው። ወደ መስኖ ልማትም ይስፋፋል ብለዋል።
ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። ከአርሶ አደሮች ጋርም ተቀራርቦ በመሥራት ዝርያውን ለማስፋት መታቀዱን ገልጸዋል።
በዓለም የሚወጡ ምርጥ ዝርያዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ይሠራልም ነው ያሉት። ምርጥ ዘር የመጠቀም ልምዳችን አሁንም ማደግ ያለበት በመኾኑ ይህን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ አንዱዓለም አያሌው የዲኬ 777 በቆሎ ምርጥ ዘር ለሦስት ዓመታት መሞከሩን እና ውጤታማነቱን ገልጸዋል።
ዝርያው ለቆላማ አካባቢዎች ተስማሚ እንደኾነም ጠቁመዋል። በመኾኑም በመኸርም በመስኖም ዝርያውን ለማልማት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን የፎገራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማት ቡድን መሪ ገብሬ ታምር የምርጥ ዘሩ ተሞክሮ በአርሶ አደሮች መወደዱን ገልጸዋል።
የባየር ላይፍ ሳይንስ ኢትዮጵያ የአማራ ክልል አስተባባሪ ደረጀ ገብረሥላሴ ድርጅቱ በአማራ ክልል በስፋት እየሠራ እና ዲኬ 777 የተባለ ምርታማ የበቆሎ ዝርያን ማውጣቱን ገልጸዋል።
ዝርያው ከባሕር ወለል በላይ ከ1ሺህ 200 እስከ 1ሺህ 800 ሜትር ድረስ መልማት የሚችል፣ ድርቅን እና በሽታን የሚቋቋም እንደኾነም አብራርተዋል። ዝርያው በሄክታር ከ80 እሰከ 100 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
የክልሉ ግብርናን ጨምሮ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ለአርሶ አደሮች እንደሚሰራጭም ነው አቶ ደረጀ የገለጹት። ሙያዊ ድጋፍም እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!