በምዕራብ ጎጃም ዞን በ15 ጤና ጣቢያዎች የላቦራቶሪ ግብዓት ለማሟላት እየተሠራ ነው።

2
ፍኖተ ሰላም:ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ የአንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጻም ግምገማ ከሁሉም ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት እና ጤና ተቋማት ኀላፊዎች ጋር በፍኖተሰላም ከተማ አካሂዷል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ኤፍሬም ክፍሌ በዞኑ በግጭቱ ምክንያት ይስተዋል የነበረውን የግብዓት ስርጭት ችግሮች በመፍታት ሁሉም ጤና ተቋማት የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ገልጸዋል።
የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በ15 ጤና ጣቢያዎች ላይ የላቦራቶሪ ግብዓት ለማሟላት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
በዞኑ የወባ ወረርሽኝን ለመግታት ባለፉት ሦሥት ወራት ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የቅድመ መከላከል ሥራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
ከፍተኛ ስርጭት ባለባቸው ሁለት ወረዳዎች ከ136 ሺህ በላይ የወባ መከላከያ አጎበር ለማኅበረሰቡ መሰራጨቱን እና በአንድ ወረዳ ደግሞ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት መከናወኑን አስረድተዋል።
ባለፉት ሦሥት ወራት በዞኑ ከ17ሺህ በላይ ሰዎች በወባ መታመማቸውን እና ሕክምና መሰጠቱም ተገልጿል። ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ስርጭቱ 73 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱም ተመላክቷል።
ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የአምቡላንስ አገልግሎት ለመስጠት እንቅፋት መፍጠሩን ያነሱት ኀላፊው ለዚህም ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በወረዳው የወባ ወረርሽኝ በስፋት የሚስተዋልባቸው ስምንት ቀበሌዎች ላይ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት በማድረግ ስርጭቱን መቀነስ መቻሉን የቡሬ ዙሪያ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰማኸኝ ንጉሤ ተናግረዋል።
ሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎችም በጸጥታ ችግር ምክንያት የተቋረጠውን የሕጻናት ክትባት ማከናወናቸውን አንስተዋል። ጽዱ ጤና ተቋማትን በመፍጠር እና የሕክምና ግብዓት በማሟላት የኅብረተሰቡን የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ ለማድረግ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ ነው።
Next articleልማት እና ሰላም የሚረጋገጠው በሕዝብ ትብብር ነው።