
ከሚሴ:ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የመስኖ ልማት ንቅናቄ፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና የገጠር ኮሪደር ማስጀመሪያ ንቅናቄ መድረክ በከሚሴ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በችግርም ውስጥ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በርካታ የግብርና ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና ከተረጅነት ለመላቀቅ ግብርና ቁልፍ መሳሪያ መኾኑን ጠቅሰዋል። በመስኖ ልማት እና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ውጤታማ ሥራ በመሥራት የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል በቀጣይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ በግብርናው ዘርፍ የማኅበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ ተገቢው ዕቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል። ለተፈፃሚነቱም ኹሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባልም ነው ያሉት።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በግብርናው ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም በመለየት መሥራት ይገባልም ብለዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ በመስኖ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ የመልማት አቅም እንዳለው ጠቅሰው ሁሉንም የውኃ አማራጮች በመጠቀም ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በቀጣይ እንደሚሠራ አስረድተዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሀሰን ሰይድ በበኩላቸው በምርት ዘመኑ በመኸር ሊታጣ የሚችለውን ምርት ለመተካት በመስኖ ልማት ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰብል በመሸፈን ከ3 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ መታቀዱን ተናግረዋል።
አዳዲስ እና ነባር ተፋሰሶች ላይ የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ በመሥራት የውኃ አማራጭን በማሳደግ የአርሶ አደሮችን ኑሮ ለማሻሻልም ይሠራል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!