የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ጭምር በማሳየት ለሕጻናት መብት ሊታገሉ ይገባል።

4

ባሕር ዳር: ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የ2018 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመጀመሪያው ሩብ ዓመት እፈጻጸም እና በቀጣይ አቅጣጫ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።

በውይይቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እንዳሉት በ2018 የትምህርት ዘመን ለመመዝገብ ከታቀደው 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ እስከ ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም ድረስ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተማሪዎችን መመዝገብ ተችሏል።

በምዝገባው በቅድመ አንደኛ 73 በመቶ፣ በአንደኛ እና መካከለኛ ትምህር ቤቶች 52 ነጥብ 5 በመቶ፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ 32 በመቶ ማከናወን መቻሉን ነው የገለጹት። አሁን ላይም የትምህርት መዋቅሩ ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት የመመዝገብ ሥራውን እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የተመዘገቡ ተማሪዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ ትምህርት ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ የባከኑ የትምህርት ጊዜያትን የማካካስ ሥራ እየተሠራ ነው። የአዳር ጥናት እና ቤተ መጽሐፍትን ቅዳሜ እና እሑድ ጭምር ክፍት በማድረግ ተማሪዎች እንዲያነቡ መደረጉንም ነው የገለጹት።

ቅዳሜን ሙሉ የትምህርት ቀን በማድረግ ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። መምህራን በሚያስተምሩት ትምህርት የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና እንዲያገኙም ተደርጓል ብለዋል።

የተማሪዎችን ሥራ የሚያሳድጉ እና ገበያውን ማዕከል ያደረጉ የሥራ እና የተግባር ትምህርቶች ጭምር እየተሠጡ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል። ተማሪዎች በራሳቸው ተማምነው ውጤት ማስመዝገብ የሚችሉበት የአፈታተን ሥርዓት ስለመዘርጋቱም ተብራርቷል። የመምህራንን ጥቅማጥቅም የማስከበር ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ኀላፊዋ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ከ2 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች በከፊል እና ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፤ እነዚህን ተቋማት መልሶ ለመገንባት ከሀገር ውጭም ኾነ በሀገር ውስጥ የሚኖሩ የሚመለከታቸው ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

መንግሥታዊ ተቋማት እንዲሁም ማኅበረሰቡ በተለይም ደግሞ ወላጆች የትምህርት ተቋማትን የመጠበቅ እና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት በተለይም ደግሞ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ጭምር በማሳየት ለሕጻናት መብት እንዲታገሉም ጠይቀዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደስታ አሥራቴ በ2018 የምህርት ዘመን ለመመዝገብ ከታቀደው ተማሪ ውስጥ እስከ አሁን 53 በመቶ መመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል። ከተመዘገቡት ውስጥ ደግሞ 81 በመቶው በመማር ላይ ይገኛሉ።

ያልተመዘገቡ ተማሪዎችን ለመመዝገብ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። የተመዘገቡ ተማሪዎችን ደግሞ በትርፍ ጊዜ ጭምር እንዲማሩ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ
ነጋልኝ ተገኘ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር በትምህርት ዘርፉ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች ሰሜን ጎጃም ዞን አንዱ መኾኑን ነው የገለጹት። በ2018 የትምህርት ዘመን ከታቀደው ውስጥ የተመዘገበው ዝቅተኛ መኾኑን ገልጸዋል።

የትምህርት ጉዳይ በማኅበረሰቡ ደረጃ አጀንዳ በማድረግ በተለይም በወላጆች እና በማኅበረሰቡ ተሰሚነት ያላቸው አባቶች ጋር በመቀናጀት የምዝገባ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ኀላፊነት ወስደው እንዲሠሩም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምሁራን ግጭትን ከምንጩ እንዲደርቅ የማድረግ ኀላፊነት አለባቸው።
Next articleየምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ ነው።