
ወልድያ:ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ሠራተኞች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ምክክር ተካሂዷል።
በምክክሩ የተሳተፉት መምህራን ሰላም በንግግር እንደሚፈታ እና ንግግርን ማስቀደም አሁን ለሚታየው የግጭት አዙሪት መፍትሔ እንደሚኾንም ጠቁመዋል።
ዓለም ከግጭት ነፃ ኾና እንደማታውቅ የገለጹት መምህራኑ ይሁን እንጂ መቋጫው ንግግር በመኾኑ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
አሁን ያለው ግጭት በሕዝብ ላይ ተጽዕኖ እያደረሰ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ለነገ የሚባል መፍትሔ ሊኖር እንደማይገባም አስረድተዋል። መፍትሔዎቹን አሁን መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።
ከመንግሥት ጋር ቅራኔ ካላቸው ጋር በነጻነት ተቀራርቦ መነጋገር ወደ መፍትሔ መሄድ እንደሚገባም አንስተዋል። ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎችን ከቀበሌ ጀምሮ መሥራት ካልተቻለ ሥራ አጥነት ግጭትን የሚያባብስ እንደኾንም ገልጸዋል።
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አበበ ግርማ (ዶ.ር) የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሁሉን አቀፍ ግንዛቤ ያዳበሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። እንደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምም እያንዳንዱን ነገር በአመክንዮ መተርጎም ይገባል ብለዋል።
የግጭቱን ምክንያት እና ውጤት ያማከለ፣ በምርምር የታገዘ የመፍትሔ ሃሳብ ማፍለቅም ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ይጠበቃል ነው ያሉት።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምሥራቅ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው መከላከያ ሀገር የመጠበቅ ኀላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ታሪክ እና የሚሠራባትን ውጫዊ አሻጥር ምሁራን እንደሚያውቁት የገለጹት አዛዡ ባዕዳን በቀጥታ ጉዳያቸውን ማስፈፀም ባለመቻላቸው በራሳችን ወገኖች አጀንዳ ተሸካሚነት ሊያስፈጽሙ እየታገሉ ነው ብለዋል።
ምሁራን የባዕዳን ተልዕኮ ያነገቡ ልጆችን መክሮ መመለስ እና የጉዳዩን አሳሳቢነት በሳይንሳዊ ትንታኔ የማስረዳት ኀላፊነት አለባቸውም ነው ያሉት።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ11ኛ እዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አድማሱ ዓለሙ መከላከያ የአካባቢውን ሰላም ለማጽናት ቁርጠኛ ኾኖ ይሠራል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ እንደልብ ተንቀሳቅሶ ማኅበራዊ ጉዳዩን እንዳይፈጽም፣ ምሁራንም ተንቀሳቅሰው የምርምር ሥራ እንዳይሠሩ የሚያደርገውን ችግር ለመቅረፍ መከላከያ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑንም ነው ያስረዱት።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ምሁራን ሳይንሳዊ መፍትሔ አፍላቂ ኾነው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይም ለግጭት ምንጭ የኾኑ ጉዳዮችን በማመላከት እና መንግሥት መሥራት ያለበትን ጉዳይ በማሳየት ግጭትን ከምንጩ እንዲደርቅ የማድረግ ሥራ እንዲሠሩም ጠቁመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!