
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 12/2018ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚያዊ እድገቷ ፈታኝ ከሆኑባት ጉዳዮች አንዱ የሯሷ የባሕር በር አለመኖር ነው። የባሕር በር አለመኖር ሀገሪቱ በዓመት በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ለወደብ አገልግሎት እንድትከፍል አድርጓታል።
በምሥራቅ አፍሪካ የጸጥታ ሁኔታ ላይም ተሳትፎ ለማድረግ ገድቧታል። ወደ ውጭና ወደ ውስጥ የሚደረጉ ቀጥተኛ የንግድ እንቅስቃሴዎቿንም ወስኖታል። ለሥራ እድል ፈጠራ አጋዥ እንዳይሆን እንቅፋት ጥሏል። ኢትዮጵያ ከፍተኛ ወጭ አፍስሳ የምታሠለጥናቸውን መርከበኞችንም ለሀገራቸው ባይተዋር አድርጎ በሌሎች ሀገራት ብቻ ተሰደው እንዲሠሩ አስገድዷል።
ከኢትዮጵያዊ ስደተኛ መርከበኞች መካከል ካፒቴን ምኒሊክ ታደሰ (የሚሠሩበት የመርከብ ድርጅት ለመገናኛ ብዙኅን መረጃ እንዲሰጡ ስለማይፈቅድ ስማቸውን ቀይረናል) አንዱ ናቸው። “ድርጅቴ የትኛውንም አይነት መረጃ ይዤ በመገናኛ ብዙኀን እንድቀርብ ባይፈቅድም ስለሀገሬ ኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ግን ችየ ዝም አልልም” በማለት ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር በበይነ መረብ ቆይታ አድርገዋል።
ካፒቴኑ በኒውዝላንድ የኬሚካል ጫኝ መርከብ ላይ ነው የሚሠሩት። አሁን ላይ በውጭው ዓለም የባሕር መርከበኛ ሁነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በዚሁ ሥራቸው ምክንያት የባሕር በር ያላቸውን በርካታ ሀገሮች የማየት እድል እንዳገኙም ነግረውናል።
በተለያዩ ጊዜያትም የተለያየ ዜግነት ካላቸው የሙያ አጋሮቻቸው እና ከመርከብ ደንበኞቻቸው ጋር የመገናኘት እድል እንዳላቸው ነግረውናል። በግንኙነታቸውም “የባሕር በር ሳይኖራችሁ እንዴት መርከበኛ ልትሆኑ ቻላችሁ?” የሚሉ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እና አግራሞቶች እንደሚገጥሟቸው ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያን ከባሕር በር ጋር ያላትን ታሪክ ያለመረዳት ችግር እንዳለም ጠቅሰዋል። በሕዝብ ቁጥር ከኢትዮጵያ የሚያንሱ የአፍሪካ ሀገሮች የባሕር በር ስላላቸው ታዋቂነታቸው ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ መርከቦችን አሰማርታ ቀይ ባሕር ላይ በርካታ የንግድ እንቅስቃሴ ስታደርግ እንደነበር ታሪክ የጠቀሱት ካፒቴኑ ዛሬ ላይ የባሕር በር ተቆልፎባት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቷ ተገድቦ፣ ልጆቿ በስደት ሲንከራተቱ እና እንዴት ወደ ሙያው ተቀላቀላችሁ የሚሉ የቅርብ ዓመታት ጥያቄዎች በብዛት ሲሰነዘሩ መስማት ተጽዕኖው ከባድ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የባሕር በር አለመኖር ሌላ ሰው ቤት በእንግድነት ሄዶ የተለያዩ አገልግሎቶችን በሰቀቀን እንደመጠቀም ነው፤ ትልቅ ጉዳትም አለው ብለዋል። ኢትዮጵያ ከዓለም ጋር የምትገናኝበትን የባሕር በር ነው በግፍ ያጣችው ብለዋል። በወደቦች አካባቢ ቀጥታ ግዥ በዶላር እንደሚከናወን፤ ግብይቱ እና የቱሪዝም እንቅስቃሴውም ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል። ይህም ለሀገራቱ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ነው ብለዋል። የባሕር በር ላሏቸው ሀገራት ብቻ የተፈቀደ ስታንደርድም አለ፤ ኢትዮጵያ ግን የተቆለፈባት ሀገር በመኾኗ የዘርፉ ተጠቃሚ አይደለችም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ከተሞች ካለው የነዳጅ ወረፋ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአብነት ጠቅሰውም መንግሥት ነዳጅ የመግዛት እጥረት ኑሮበት ሳይሆን ወደብ አካባቢ ባሉ ሁኔታዎች የሚፈጠሩ መጓተቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሹፌሮች እና ተሽከርካሪዎች ረጅም ርቀት ተጉዘው ከሄዱም በኋላ በኪራይ ወደብ አካባቢ የሚቆሙበት ሁኔታ ትልቅ የኢኮኖሚ ኪሳራ መሆኑንም ተናግረዋል። ወደብ ቢኖር ግን ቀጥታ ለሕዝብ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች በጊዜ መምጣት ይችላሉ ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ግንኙነትን ማጠናከር ብቻ ሳይሆን የቱሪዝምና የቀጠናውን ደህንነት በጋራ የመጠበቅ ጉዳይም መሆኑንም ነው የተናገሩት። የአንድ ሀገር የባሕር በር መኖር አየር ኃይሏን በወደቦች አቅራቢያም ለማስፋፋትና ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።
ቀይ ባህር አካባቢ በአማጺያንና በዘራፊዎች ምክንያት የሰላም መታወክ የሚስተዋልበት ሁኔታ መኖሩን አንስተው በር አልባዋ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ቀጠና ደህንነት በባለቤትነት ከማስጠበቅና አማጽያኑን ከመቆጣጠር አኳያ ለዓለም የምታበረክተው አስተዋጽኦ ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
የባሕር በር ኢትዮጵያ የራሷን ወታደራዊ አቅም እና ሉዓላዊነት ለማሳደግ ያስችላታል ነው ያሉት። ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶቿንም እንደሚያፋጥን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከዓለም ጋር የተቀላጠፈ ግንኙነት ሲኖራት እና አስተዋጵኦም ስታደርግ ታዋቂነቷ እንደሚጨምርም ጠቅሰዋል።
ወደብ ቢገኝ ኢትዮጵያ ምን ልትሆን እንደምንችል እንደ አንድ ኢትየጵያዊ የፈጠረባቸውን ቁጭት እና ጉጉትም አጋርተውናል። የባሕር በር ማጣት ሙሉ አካል ያለው ሰው የሆነ የአካል ክፍሉ እንደጎደለው ያህል ስሜት እንዳለውም ጠቅሰዋል። በመላው ዓለም ተዘዋውረው ካዩት ምልከታ ተነስተውም ሁለንተናዊ ከፍታ እንደሚኖራት ጠቅሰዋል። በቆዳ ስፋታቸውና የሕዝብ ብዛታቸው ትንሽ የሆኑ ሀገሮች ጨምሮ ወደ ብዙ ሀገራት ኬሚካሎችን፣ የተለያየ አይነት የኢንዱስትሪ ምርቶችን እና ማሽነሪዎች እንደሚጭኑም ተናግረዋል። እነዚህ ሀገራት በኢንዱስትሪው ዘርፍ የላቁት የባሕር በር ስላላቸውና ኢኮኖሚያቸው ስለተነቃቃ ነውም ብለዋል።
የባሕር በር ቢኖራት ኢትዮጵያም ኢንዱስትሪዎቿ ይስፋፉ ነበር ሲሉ በቁጭት ሀሳባቸውን አካፍለውናል። ወደብና ቴክኖለጅ የተያያዙ ነገሮች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። ማንኛውም ሀገር ሙሉ ነገሩን ከሀገሩ አያገኝም፤ ያለውን ይሰጣል የሌለውን ከሌሎች ያመጣል ነው ያሉት። ሰጥቶ መቀበል መርህ በኾነበት በዚህ ዘመን የባሕር በር አለመኖር ትልቅ ሀገራዊ ፈተና እና የህልውና ጉዳይ ነውም ብለዋል።
አንድ ሀገር ወደብ አላት ማለት ባለሀብቶች፣ ኢንቨስተሮች፣ ነጋዴዎች በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሊያዋጡ የሚችሉ ነገሮች በሀገራቸው ወደብ ላይ ተገናኝተው ከሌሎች ሀገሮች ካምፖኒዎች ጋር የሚገናኙበትና ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚያቀላጥፋበት እድል ይፈጥራል ብለዋል። የባሕር በር መኖር ለሀገሪቱ ሕዝብ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በሦሥተኛ ወገን ሳይሆን በቀጥታ ለማግኘት እንደሚያግዝም ተናግረዋል። መርከበኞችና ኢንቨስተሮች ወደ ወደቡ በመጡ ቁጥር ሀገሪቱን እንዲጎበኙ ያደርጋልም ነው ያሉት። ያላቸውን መዋዕለ ንዋይ እንዲያፈሱም በር ይከፍታል ብለዋል። የሀገሪቱን ምንዛሬ ከመጨመር አንጻርም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።
“የባሕር በር የሌላት ሀገር ሕዝብ በር በሌለው ቤት እንደሚኖር ቤተሰብ ይቆጠራል” ሲሉ ገልጸዋል ካፒቴኑ። የቤት በር ከተቆለፈ የግድ በመስኮት በኩል መውጣትና መውረድን ይጠይቃል፤ ኢትዮጵያም እንዲሁ የባሕር በር ተቆልፎባት በኪራይ ወደብ እየማቀቀች ትገኛለች ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በርካታ መርከቦችን በገዛ ባሕር በሯ ስታስተናግድ የቆየች የባሕር ላይ ባለታሪክ መኾኗን ጠቅሰው አሁን ላይ ግን መርከበኛ ልጆቿ ሁሉ በባዕድ ሀገር መርከቦች ላይ እንድንሰማራ ተገደናል ነው ያሉት።
ሕልመኛዋ ሀገር የባሕር በር የለኝም ብላ እጇን አጥፋ አልተቀመጠችም፤ በዓለም ፊት እና በባሕሩ ላይ ሁሉ ተፈትነው የማያሳፍሩ መርከበኞችን እያሠለጠነች ነው፤ የባሕር ኃይልም አቋቁማለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ከዓለም ጋር በቀጥታ የምትገናኝበት እና የራሷን ልጆች አሰማርታ የምታዝዝበት የባሕር በር ያስፈልጋታል ብለዋል። ኢትዮጵያውያ ብዙ ከፍላ ያሠለጠነቻቸው መርከበኛ ልጆቿ ለሷም ሊሠሩ እንጅ በዓለም ላይ ተበትነው ሊጠፉ እንደማይገባም ተናግረዋል።
“ምድር ላይ ያሉ ሰዎች ባሕር ላይ የምንውለውን ካፒቴኖች ያህል ስለወደብ ጥቅም አይገነዘቡ ይኾን?” ሲሉ ያጠየቁት ካፒቴኑ ኢትዮጵያውያን የባሕር በር ጥያቄ ሲነሳ አቅልለው ማየት እንደሌለባቸው መክረዋል። ይልቁንም ጉዳዩ ከኢኮኖሚ፣ ከማኅበራዊ እና ከፖለቲካዊም ጉዳይ አልፎ የደህንነት እና የሕልውና ጉዳይ ጭምር መኾኑን በውል መረዳት ይገባል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን እና የቀደመ ገናናነቷን እንድትመልስም በጋራ ቁሞ አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት ማድረግ ይበጃል ብለዋል ካፒቴኑ።
መርከበኞችን የሚያሠለጥኑ ትምህርት ተቋማትም በቁጥር እና በጥራትም ጨምረው በኢትዮጵያ እንዲስፋፉ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ካፒቴን ሚኒሊክ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን