ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የልማት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን የደሴ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

4

ደሴ: ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ አሥተዳደር በ2018 በጀት ዓመት የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ እና የመልካም አሥተዳር ሥራዎችን ለማከናወን ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል፡፡

በዚህም የኮሪደር ልማት ሥራ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ የአስፓልት ሥራ፣ በአዲስ መልክ የሚሠሩ የመንገድ ሥራዎች፣ ለማኅበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት የሚሰጥ የአንድ ሞሶብ ግንባታ እና በርካታ ሥራዎች ይከናወናሉ ተብሎ ዕቅድ ተይዟል፡፡

ዛሬ የከተማዋ ማኅበረሰብ እና የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት የበጀት ዓመቱ የልማት ሥራዎች የተግባር ምዕራፍ የማስጀመያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

አሚኮ ያነጋገራቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ደሴ ከተማ ለዓመታት ልማት ርቋት መቆየቷን በማንሳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ከተማዋን የሚመጥኑ እና ማኅበረሰቡን ያሳተፉ በመኾናቸው በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መኾናቸውን ነው የጠቀሱት፡፡

የሚሠሩት የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው መርሐ ግብር እየተጠናቀቁ መኾናቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የደሴ ከተማ አሥተዳደር መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አሥኪያጅ አንዱዓለም እሸቱ በከተማው የመንገድ ተደራሽነትን በማስፋት የከተማውን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የመንገዶቹ ግንባታ የኅብረተሰቡን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ የሚመልሱ በመኾናቸው በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ በጥራት እንዲጠናቀቁ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

መንገዶቹን በጥራት ከማጠናቀቅም ባለፈ ከሌሎች የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ጋር በቅንጅት የመሥራት ልምድ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡

የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ከተማ አሥተዳደሩ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍን በማጠናቀቅ ማኅበረሰቡን አሳትፎ ወደ ተግባር ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልጸዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ በ2018 በጀት ዓመት በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ለማከናወን በጀት መመደቡን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ለከተማዋ ዕድገት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ የልማት ሥራዎችን ለመተግበር መሪዎች በቁርጠኝነት እየሠሩ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ማኅበረሰቡ በልማቱ የሚያደርገውን ድጋፍ እና ክትትል አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፦ደጀን አምባቸው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት መንገደኞችንም ኾነ አሽከርካሪዎችን ከእንግልት እና ከሕገ ወጥ ሥራ ታድጓል።
Next article“የባሕር በር የሌላት ሀገር ሕዝብ፣ በር በሌለው ቤት ውስጥ እንደሚኖር ቤተሰብ ይቆጠራል” ኢትዮጵያዊው ካፒቴን