የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት መንገደኞችንም ኾነ አሽከርካሪዎችን ከእንግልት እና ከሕገ ወጥ ሥራ ታድጓል።

4
ፍኖተ ሰላም:12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በዞኑ በአራት ከተሞች የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት እየተሰጠ መኾኑን የዞኑ ትራንስፖርት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ ወርቅነህ መንግሥት ገልጸዋል።
አገልግሎቱም የተሳፋሪዎችን እንግልት እና ከታሪፍ በላይ ይጠየቁ የነበረውን ክፍያ ያስቀረ መኾኑን አስረድተዋል።
በተለይ ተሽከርካሪዎች መያዝ ከሚገባቸው በላይ በመጫን የሚከሰተውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
የተጀመረውን የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማሳለጥ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ዘርፉ የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ በመኾኑ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እና የተሳፋሪዎችን እንግልት ለመቅረፍ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል።
የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎቱን በሌሎች አካባቢዎችም ለማስፋት እየተሠራ መኾኑን የገለጹት ተወካይ ኀላፊው የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን በመገንባት የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱንም ተናግረዋል።
በፍኖተሰላም መናኾሪያ አሚኮ ያገኛቸው አስተያየት ሰጭ አሽከርካሪ ሰለሞን በላይ ከዚህ በፊት ከመናኾሪያ ውጭ በመውጣት ተሳፋሪ በመጠባበቅ ጊዜ ያባክኑ እንደነበር እና በተቆራራጭ በመጫን ተሳፋሪዎችን እና አሽከርካሪዎችን ለእንግልት ይዳርጋቸው እንደነበር ገልጸዋል።
የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎቱ ግን በመርሐ ግብር መሠረት በመጫን የነበሩ ችግሮችን የቀረፈ መኾኑን አስረድተዋል።
ሌሎች አስተያየታቸውን ያጋሩን ተሳፋሪዎች በበኩላቸው ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ከታሪፍ በላይ ክፍያ ይጠየቁ እንደነበር እና ከመጠን በላይ ተሳፋሪ ስለሚጫን ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ እነዚህ ሁሉ ችግሮች መፈታታቸውን እና በዚሁም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous article“በዚህ ዓመትም 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አልመጡም”
Next articleከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የልማት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን የደሴ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።