
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአፍሪካ የኮሮናቫይረስ አሳሳቢነት በፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱ 43 ሀገራት ድንበሮቻቸውን ሙሉ በሙሉ መዝጋታቸውን የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል አስታውቋል፡፡
እንደ ማዕከሉ መግለጫ እስከ ትናንት ቅዳሜ ድረስ በአህጉሩ 225 ሺህ 126 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል፤ 6ሺህ 51 ለኅልፈት ተዳርገዋል፤ 102 ሺህ 912 ሰዎች አገግመዋል፡፡ የሰሜኑ የአፍሪካ ክፍል ደግሞ ወረርሽኙ ይበልጥ እየተስፋፋበት መሆኑ ታውቋል፡፡
በተወሰኑ ሀገራት ትናንት የተመዘገቡ የምርመራ ውጤቶች ከእስካሁኖቹ ከፍተኛ መሆናቸው የቫይረሱን ስርጭት አሳሳቢነት እንደሚያመላክትም ማዕከሉ አሳስቧል፡፡ ግብጽ በ24 ሰዓታት 1 ሺህ 677 ሰዎች አዲስ በቫይረሱ እንደተያዙባት ማረጋገጧንና ይህም ወረርሽኙ በሀገሪቱ ከተከሰተ የተመዘገበ ከፍተኛው አሐዝ መሆኑን ማሳወቋ ይታወሳል፡፡ በግብጽ በቫይረሱ የተያዙት ቁጥር 42 ሺህ 980 መድረሱን፣ ከእነዚህ መካከል 1ሺህ 484 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ከአህጉሩ ወረርሽኙ በአስከፊ ደረጃ በተሠራጨባት ደቡብ አፍሪካም 65 ሺህ 736 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ 1ሺህ 423 ሰዎች ደግሞ ለኅልፈት ተዳርገዋል ይላል የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ፡፡
ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛቷ ሁለተኛዋ ኢትዮጵያም ትናንት ከእስካሁኑ ከፍተኛውን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አሐዝ ማስመዝገቧ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ትናንት ብቻ 268 ሰዎች በኮሮናቫይረስ እንደተያዙ መገለጹ ይታወሳል፤ በዚህም እስከ ትናንት ሰኔ 6/2012 ዓ.ም ድረስ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 3 ሺህ 166 ደርሷል፤ 55 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ወረርሽኙ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን ተከትሎም 43 የአፍሪካ ሀገራት ሙሉ በሙሉ ድንበሮቻቸውን መዝጋታቸውን የሲ ጂ ቲ ኤን ዘገባ አመላክቷል፡፡ ከእነዚህ ሀገራት መካከል 35 የሚሆኑት ደግሞ ድንበሮቻቸውን ከመዝጋት ባለፈ የምሽት ሰዓት እላፊ እንቅስቃሴ እገዳ መጣላቸው ታውቋል፡፡
የአህጉሩ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል እንደገለጸው 18 ሀገራት ኅብረተሰቡን በስፋት መመርመር ጀምረዋል፤ 41 ሀገራት ደግሞ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀምን አስገዳጅ አድርገዋል፡፡
በአስማማው በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡