ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የተፋሰስ ልማትን መጠቀም ወሳኝ ነው።

4
ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የዞኑን የመስኖ ልማት እና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
የሰሜን ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን ባለፈው ዓመት የነበረው የመስኖ እና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ውጤት የተገኘበት መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ዓመቱ በነባር መስኖ ከ24ሺህ 300 ሄክታር መሬት በላይ፣ በአዲስ መስኖ ደግሞ ከ19ሺህ 500 ሄክታር መሬት በላይ የለማበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በዚህም የታቀደውን ዕቅድ ማሳካት መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡
የዛሬው መድረክም በ2018 በጀት ዓመት በመስኖ እና በተፈጥሮ ሃብት ልማት በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡ ከመስኖ ልማቱ ማግኘት የሚጠበቅበትን ውጤት እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል እንደኾነም አንስተዋል።
የመስኖ ልማት እንደ ሀገር በምግብ ራስን ለመቻል ከሚደረጉ የግብርና ሥራዎች አንዱ መኾኑንም አስረድተዋል። ያለውን ሃብት በመጠቀም እና ጠንክሮ በመሥራት ሉዓላዊት ሀገር መፍጠር ይገባልም ብለዋል፡፡
የሰሜን ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ በለጠ ጥጋቡ ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር የመስኖ ልማት እና የተፋሰስ ሥራዎችን መሥራት የግድ መኾኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት በተሠሩ የተፋሰስ ሥራዎች ውጤት መምጣቱንም አስታውሰዋል።
በዞኑ 1ሽህ 333 ተፋሰሶች መኖራቸውን የተናገሩት ምክትል አሥተዳደሪው ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የተፋሰስ ልማትን መጠቀም ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት 466 ተፋሰሶችን ወደ ተግባር ለማስገባት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በተያዘው ዓመትም ያለውን አቅም አሟጦ በመጠቀም የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ 33ሺህ 543 ሄክታር መሬት በመስኖ እንደሚሸፈን ተናግረዋል፡፡ከዚህ ውስጥ ደግሞ 21ሺህ ሄክታር መሬቱ በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚለማ ነው ያስረዱት፡፡
ይህንን ውጤታማ ለማድረግም 9ሺህ የውኃ መሳቢያ ሞተሮች፣ 56 ዘመናዊ ካናል፣ ቆጋን ጨምሮ በዞኑ የሚገኙ ወንዞችን በመጠቀም የታቀደውን ዕቅድ ውጤታማ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ብቻ 63 ሺህ ኩንታል የዳፕ እና የዩሪያ ማዳበሪያ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡የዘር ችግር እንዳይኖርም ይሠራል ነው ያሉት።
በመስኖ ሥራው ላይ 80 ሺህ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል፡፡
የሰሜን አቸፈር ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ንጉሥ አለነ በ2018 በጀት ዓመት በ57 ተፋሰሶች 139 ሄክታር የአፈር እና የውኃ ጥበቃ ሥራ ለመሥራት ዕቅድ ተይዟል ብለዋል።
የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ እና ሕጋዊ ሰውነትን ለመስጠት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደሳለኝ አድማሴ ወረዳው የመስኖ ልማት ሥራን በመሥራት ሰፊ ልምድ እንዳለው ተናግረዋል።
11ሺህ 134 ሄክታር መሬትን በማልማት 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅደው እየሠሩ መኾናቸውን አስታውቀዋል።
7ሺህ 480 ሄክታር የሚኾነው በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የሚሸፈን መኾኑን ገልጸዋል። ሌሎች በአካባቢው ለገበያ የሚውሉ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን እንደሚያመርቱም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
Previous articleየቻይና ቴክኖሎጂ እና ፈጠራን ከኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ጋር በማስተሳሰር ለጋራ ልማት መሥራት ይገባል።
Next articleበፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ እና በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ የከባድ መኪኖች መገጣጠሚያ ሊገነባ ነው።