የአርሶ አደሮች ቴክኖሎጅን የመጠቀም ፍላጎት ጨምሯል።

3
ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎በኢትዮጵያ ትክክለኛ የምርት አሰባሰብ ሂደትን ባለመከተል የግብርና ምርት እንደሚባክን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህንን ብክነት ለመከላከል የሰብል መሰብሰቢያ ማሽን መጠቀም ዋነኛ መፍትሔ እንደኾነም ይነገራል፡፡
‎በምሥራቅ ጎጃም ዞን የባሶ ሊበን ወረዳ አርሶ አደሮች የስንዴ ምርታቸውን ለመሰብሰብ ከአምስት ዓመት በፊት ጀምሮ በኮምባይነር የመሰብሰብ ልምድ እንዳላቸው ነግረውናል፡፡ ኮምባይነሩ በባለሃብቶች እና በአርሶ አደሮች ዩኒየን አማካኝነት በግብርና ጽሕፈት ቤት በኩል ተመቻችቶ አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ገልጸዋል፡፡
‎በባሕላዊ መንገድ ስንዴን ሲሰበስቡ ከፍተኛ ጉልበት እና ጊዜ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። የስንዴ ነዶ ሲሰበሰብ በዝናብ እና በምስጥ ጉዳት ይደርስበታል፤ ብዙ ጉልበት እና ጊዜ የሚፈልግ፣ ምርቱ ጥራትም ላይ ችግር የሚፈጥር ነበር ነው ያሉት።
‎በኮምባይነር ሲሰበሰብ ስንዴው ማሳው ላይ እንዳለ አጭዶ ምርት እና ገለባውን ለይቶ ጥራት ያለው ምርት ማግኘት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ በፊት እስከ አንድ ሳምንት ጊዜ ይጨርስ የነበረው በሁለት ሰዓታት ውስጥ ይጠናቀቃል ነው ያሉት፡፡
‎ጥራት ያለው እና በቂ ምርት ገበያ ላይ እንዲኖር የኮምባይነር ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ይህም በአሰባሰብ ወቅት የሚባክነውን ምርት ይቀንሳል፤ ቢያንስ በሄክታር ከ3 እስከ 4 ኩንታል ከብክነት ይታደጋል ነው ያሉት፡፡
‎ኮምባይነር በሁሉም ቦታ ያለመድረስ ችግር መኖሩንም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመት በወረዳው የስንዴ ምርት ከፍተኛ ነው፤ ለዚህ ምርት መሰብሰቢያ በቂ ማሽን እንዲቀርብላቸውም ጠይቀዋል፡፡
‎በምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ እምቢያለ አለኸኝ በ2017/18 የምርት ዘመን 25 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የስንዴ ሰብልን በቴክኖሎጅ በመታገዝ በኮምባይነር እንደሚሰበሰቡ ተናግረዋል፡፡
በዞኑ የግለሰቦች እና የዩኒየኖች ኮምባይነር በኪራይ ለአርሶ አደሮች አገልግሎት እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡ የበቆሎ መፈልፈያም ማሽንም በተለያዩ ቦታዎች መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡
‎ሰብል በኮምባይነር መሰብሰብ የምርትን ጥራት መጠበቅ እንደሚያስችል ጊዜ እና ጉልበት እንደሚቆጥብ ገልጸዋል። በአርሶ አደሮች ኮምባይነርን የመጠቀም ሰፊ ፍላጎት በመኖሩ ለተደራሽነቱ ከባለቤቶች ጋር በመነጋገር እንደሚመቻች ጠቁመዋል፡፡
‎የጤፍ ሰብል ለመሰብሰብ ከሰብሉ ባሕሪ አንጻር ውጤታማ ቴክኖሎጅ አልተገኘም፡፡ ታጭዶ ከተሰበሰበ በኋላ ለመውቃት የሚያስችል ማሽን መኖሩን እና ጥቅም ላይ እየዋለ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
‎ሌሎች በባሕላዊ መንገድ የሚሰበሰቡ ምርቶችን አርሶ አደሮች ሰብሉ ወቅቱ ሳያልፍ መሰብሰብ አለባቸው ብለዋል። ሲከመርም በምስጥ እንዳይበላ ከመሬት ከፍ አድርጎ መኾን አለበት ነው ያሉት። ሲወቃም ሸራ በመጠቀም የምርቱን ጥራት ማስጠበቅ እና እንዳይባክን እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።
‎በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የድህረ ምርት ቴክኖሎጅ ባለሙያ ምትኩ መላኩ የመኸር ምርትን ከብክነት ነጻ አድርጎ መሰብሰብ ምርት እና ምርትማነትን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል፡፡ ለዚህም በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች አርሶ አደሮች በተገቢው መንገድ ምርትን በወቅቱ እንዲሰበሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
‎ምርት በደረሰበት በትክክለኛው ጊዜ፣ አስፈላጊውን የሰው ኀይል እና መሳሪያ በማዘጋጀት መሰብሰብ አለበት ነው ያሉት፡፡
‎በክልሉ አርሶ አደሮች ቴክኖሎጅ የመጠቀም ፍላጎት ጨምሯል ያሉት ባለሙያው በምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም እና በሰሜን ሸዋ ዞን ላይ ስንዴ በኮምባይነር ይሰበሰባል ነው ያሉት፡፡
‎የመውቂያ ማሽኖች ለጤፍ፣ ለበቆሎ፣ ማሽላ እና ሩዝ በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው ብለዋል፡፡ ይህም የምርቱን ጥራት በማስጠበቅ ጊዜ እና ጉልበትን ይቆጥባል ነው ያሉት።
‎ የባንክ ብድር አቅርቦት እየተመቻቸ ባለሃብቶች አገልግሎቱን ለአርሶ አደሮች እንዲያቀርቡ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
‎አርሶ አደሮች ሰብሉን በትክክለኛ በደረሰበት ጊዜ ወቅቱን ጠብቀው ከአፈር ንክኪ ነጻ አድርገው እንዲሰበስቡ እና በሚጓጓዝበት ጊዜም አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
በአማራ ክልል በምርት ዘመኑ ከ187 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሕግን ያከበረ የነዳጅ ግብይት እንዲኖር እየተሠራ ነው።
Next articleዘመናዊ የባቡር መስመሮችን በመዘርጋት ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እየተሠራ ነው።