
ጎንደር: ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት ተግባራት አፈጻጸም ግምገማ እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እያካሄደ ነው።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው “አሁን ላለንበት ቀውስ መውጫ ቁልፉ ልማት ነው” ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ከጸጥታ ሥራዎች ጎን ለጎን የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አስረድተዋል።
ከግል ፍላጎቶች እና ከትናንሽ እርካታ ወጥቶ ለኀብረተሰቡ የሚጠቅሙ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
መሪ ቀድሞ አይቶ ለኅብረተሰቡ የሚያሳይ መኾን አለበት ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ለዚህ የሥራ ኀላፊዎች ራሳቸውን ማብቃት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
መሪዎች ለሀገር ልማት ግንባታ መሥዋት መክፈል እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በጎንደር ከተማ ቆይታቸው ውጤታማ ተግባራትን ማየታቸውን አንስተዋል። የጎንደር የመፈጸም አቅም፣ የሥራ ባሕል ለውጥ እና የፈጠራ ሥራ ማሳያ መኾናቸውንም ጠቅሰዋል።
በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት ለመፍታት የጋራ ሥራዎችን በአብሮነት መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሥጣጥን ምቹ እና ቀልጣፋ ለማድረግ ተቋማትን ማዘመን እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
ሥራዎችን በውጤታማነት ለመፈጸም የሥራ ኀላፊዎች የክትትል ሥራዎችን መሥራት እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
በቀውስ ውስጥ ኾኖ የልማት ሥራዎችን የማስቀጠል ባሕልን ማዳበር እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
ዘጋቢ :- አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!