ዋድላ በአለትም ይቀኛል፡፡

576

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 07/2012 ዓ.ም (አብመድ) ቱሪዝም በኮሮናቫይረስ የተቀዛቀዘውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማንቂያ እንዝርት እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ከጫማ አሳማሪዎች እስከ ሪዞርትና ሆቴል ባለቤቶች ድረስ ያሉ የዘርፉ ተዋንያን ኪስ ያሞቃል፡፡ ቱሪዝሙ አሁን ካለበት ደረጃ ለማሳደግ ጎብኝዎች የመግቢያ ትኬት ቆርጠው ወደቅርሶቹ እንዲገቡ ብቻ ሳይሆን እንደየመዳረሻዎቹ ልዩነት የተለያዩ የአለባበስ እና የአጋጊያጥ መመሪያዎችን እንዲከተሉ ማድረግ ደግሞ የበለጠ ገበያ ይፈጥራል፡፡ በመዳረሻ አካባቢዎች አለባበሶች በአስገዳጅ መመሪያዎች ቢታገዙ ከዘርፉ አሁን ከሚገኘው ገቢ በእጥፍ ማግኘት እንደሚቻል አብመድ በተደጋጋሚ ዘግቧል፡፡
እንደዳግማዊ ላልይበላ ዓይነት አዳዲስ የመስህብ ሀብቶች ለጎብኝዎች መዳረሻነት በሮቻቸው ሲከፈቱ ደግሞ ቱሪዝም ሀገሪቱ ለምታደርገው የብልጽግና ጉዞ የኢኮኖሚ ምሰሶነቱ እንዲያድግ ያግዛሉ፡፡

ዳግማዊ ላልይበላ በሰሜን ወሎ ዞን ዋድላ ወረዳ ከጋሸና በአራት ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ አዲስ ፍልፍል አብያተ ክርስትያናት መገኛ ነው፡፡ አምባ እግር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያለው ዳግማዊ ላልይበላ ሰኔ 25/2003 ዓ.ም በአካባቢው ነዋሪዎች የላልይበላ ዋሻ ተብሎ ይጠራ ከነበረ ስፍራ የተሠራ አምሳለ ላልይበላ ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ‘‘ቅዱስ ላልይበላ አንድ ወቅት ጀምሮ የተወው ነው፤ ጊዜው ሲደርስ ይሠራል’’ ብለው ያምኑ እንደነበር ከዋድላ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ በመርጌታ ገብረመስቀል ተሰማ አነሳሽነት በሦስት ሰዎች አማካኝነት 10 አብያተ ክርስትያናትን ለመሥራት ታቅዶ አራት ተጠናቅቀዋል፤ ለምዕመናን እና ጎብኝዎችም ክፍት ሆነዋል፡፡

No photo description available.

በአንድ በር የተሰናሰሉት አራቱ ቤተ መቅደሶች ሲታነጹ እያንዳንዷ ውቅር መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ወንጌል ላይ ተመሥርቶ የተሠራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ካርታ እና የመስቀል ቅርጽ ደግሞ ‘ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዜአብሔር ትዘረጋለች’ ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ተሳስሮ ቀርቧል፡፡ ረቅቆ ተከስቷል፤ ተከስቶ በጣም ረቅቆ ቀርቧል፡፡ ለሚቻላቸው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን አለት ላይ ማንበብ እንዲቻል ሆኖ ተወቅሯል፡፡ ፍልፍል አብያተ ክርስትያናቱ ክርስትያናዊ አስተምህሮን፣ ትናንትን እና መጻዒ ትንቢት እንደተመላከቱማች ታውቋል፡፡ የውቅራቸው ቅኔያት ለተመልካቾች ውበት፣ ለአዋቂዎች ትርጉምን እና ምስጢርን፣ ለአማኞች ደግሞ ምሕረትን እና ድኅነትን አዝለዋል፡፡

የዋድላ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ አዕመረ አወቀ ‘‘ከቅዱስ ያሬድ ቅኔ ድርሰት ቀጥሎ ቅኔን በኢትዮጵያ ያጸኑት የዮሐንስ ገብላዌ ልጆች ዛሬም ሀገረ ዋድላ ላይ አምሳ ላልይበላን በመድገም ታሪክን እያስቀጠሉ ነው’’ ብለዋል፡፡

No photo description available.

ኢትዮጵያውን በእጆቻቸው አለትን እንደዳቦ ቆርሰው ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሚችሉ ለሚጠራጠሩ እና የተንሻፈፈ ታሪክ ለማስተላለፍ ለሚጥሩት ሁሉ የዳግማዊ ላልይበላ ይፋ መደረግ የኢትጵያውያንን የቆየ ልምድ ያጸናዋል ነው ያሉት፡፡

በዩኒስኮ እንዲመዘገብ በሂደት ላይ የሚገኘው ዳግማዊ ላልይበላ ቀሬ 6 አብያተ ክርስትያናትም በቀጣይነት እንደሚሠሩ ይጠበቃል፡፡
የዋድላ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ ተመሥገን አምባቸው በዳግማዊ ላልይበላ ቅርስ አካባቢ ለጎብኝዎች ምቹ የሆኑ ሎጂዎች እንዲገነቡ ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶች ለመሥጠት የቦታ ችግር እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡ ወደቅርሱ የሚያስገባ ምቹ መንገድ እንዲኖርም በኅብረተሰቡ እና በወረዳው አቅም ለመሥራት ማጥናታቸውን ገልጸዋል፡፡

ታሪክ በዳግማዊ ላልይበላ እውን ሲሆን ታሪክ ሠሪዎችና ዘመነኞች ደግሞ ስማቸው በስልጣኔ የታዋጀ ክብርን ይጎናጸፋሉ፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየአሜሪካ ዶላር ቅቡልነት ማክተሚያ እየተቃረበ መሆኑን ብሎምበርግ ዘገበ፡፡
Next articleበአፍሪካ የኮሮናቫይረስ አሳሳቢነት እየጨመረ መሆኑን የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል አስታወቀ፡፡