ስለ ንግድ ምልክት ምን ያህል ያውቃሉ ?

5

ባሕር ዳር: ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የንግድ ምልክት አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ከሌላው ምርት እና አገልግሎት እንዲለይ ለማስቻል ጥቅም ላይ የሚውል ልዩ ምልክት ነው፡፡

የንግድ ምልክት ጠቀሜታው ሸማቹ ኀብረተሰብ የሚፈልገውን ምርት እና አገልግሎት በቀላሉ ለይቶ እንዲገዛ ያስችለዋል። በሚገዛው ምርት እና አገልግሎት ጥራት ላይ መተማመን እንዲፈጥርም ያደርጋል፡፡

በገበያ ላይ ተገቢ ያልኾኑ የንግድ ውድድሮችን ለመግታት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። በማመሳሰል የሚሠሩ እና ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ለመከላከል አይነተኛ መሣሪያ በመኾን ያገለግላል፡፡

የአምራች ባለቤቱን ለምርቱ መለያ ኾኖ በማስተዋወቅ የገንዘብ ትርፍን ያስገኛል። የንግድ ምልክቶች በራሳቸው ዋጋ ያላቸው በመኾኑ ክፍያን መሠረት አድርጎ ሦስተኛ ወገን እንዲጠቀምበት የመፍቀድ መብትንም ይሰጣል፡፡

በሀገራችን የንግድ ምልክትን ሥርዓት ባለው መልኩ ለመጠቀም በሕጋዊ መንገድ ማስመዝገብ እና የሕግ ከለላ ማግኘትን ይጠይቃል። ይህንን ለመፈጸም እና ለማሥፈጸም ሲባልም የንግድ ምልክት ምዝገባ እና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 501/1998 መውጣቱን በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕግ ባለሙያ ፍቅር በለጠ ያስረዳሉ።

እንደ ሕግ ባለሙያዋ ማብራሪያ የንግድ ምልክት ቃላትን፣ ዲዛይኖችን፣ ፊደላትን፣ ቁጥሮችን፣ ቀለማትን ወይም የዕቃዎችን ወይም የመያዣዎቻቸውን ቅርፅ ወይም የእነዚህን ቅንጅት ሊይዝ ይችላል፡፡

አንድን የንግድ ምልክት ሳያስመዘግቡ መጠቀም በምልክቱ ላይ በሚኖሩ የይገባኛል ክርክሮች ላይ በቀላሉ ውሳኔ ለመስጠት እንደሚያስቸግርም ነው የገለጹት። የንግድ ምልክት መብት ለመጠበቅ በጊዜያዊነት የሚሰጡ እርምጃዎች፣ የፍትሐብሔር እና የወንጀል ቅጣቶች በአዋጁ መደንገጋቸውንም አመላክተዋል፡፡

በአዋጁ ጥበቃ ያገኘን ባለመብት የሚጥስ ተግባር በተፈጸመ ጊዜ ፍተሻን እና እቃ መያዝን የሚመለከቱ የፍትሐብሔር እና የወንጀል ሥነ ሥርዓት የሕግ ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት እንደሚኖራቸውም በአዋጁ አንቀጽ 39 ላይ መደንገጉን ነው የሕግ ባለሙያዋ ያብራሩት።

በተመሳሳይ በአዋጁ አንቀጽ 40 እና 41 ላይም ይህንን የተመለከቱ የፍትሐብሔር እና የወንጀል ተጠያቂነት መደንገጉን አስረድተዋል። በዚህም መሠረት:-

👉 አንድ የንግድ ምልክት ያስመዘገበ ባለመብት ምልክቱን ሌላ አካል ቢጠቀምበት እና በማስረጃ የተደገፈ ክስ ቢያቀርብ ሥልጣን የተሰጠው ፍርድ ቤት ጊዜያዊ እግድን ጨምሮ ሌሎችንም እርምጃዎች መውሰድ እንደሚችል አዋጁ ይፈቅዳል።

👉 ፍርድ ቤቱ በፍትሐብሔር እና በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጎች መሠረት ፍተሻ እንዲካሄድ እና እቃዎች እንዲያዙ የማድረግ ሥልጣንም ተሰጥቶታል። የመብት መጣሱን ድርጊት እንዲያቆም የማዘዝ እና በባለመብቱ ላይ ለደረሰው ጉዳት ካሳ መወሰን እንደሚችል በአዋጁ ተመላክቷል፡፡

👉 በአዋጁ ጥበቃ ያገኘ መብትን ኾነ ብሎ የጣሰ ማንኛውም ሰው ከ5 ዓመት በማያንስ እና ከ10 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እሥራት እንደሚያስቀጣ ተገልጿል፡፡

👉 በወንጀል ሕግ የበለጠ ቅጣት የሚያስቀጣ ካልኾነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ጥበቃ ያገኘ መብትን በጎላ ቸልተኝነት የጣሰ ማንኛውም ሰው ከ1 ዓመት በማያንስ እና ከ5 ዓመት በማበልጥ ጽኑ እሥራት እንደሚያስቀጣ በአዋጁ ተቀምጧል፡፡

👉 ተመሳስሎ የተሠራ ወይም የተቀዳ የንግድ ምልክት ያለበትን ምርት ያከፋፈለ፣ የሸጠ ወይም የመሳሰሉትን ተግባራት የፈጸመ ሰው በተመሳሳይ የእሥራት ቅጣት እንደሚያስቀጣ ተመላክቷል፡፡

👉 አግባብነት ባለው ጊዜ ቅጣቱ ወንጀሉን ለመፈጸም ያገለገሉ ቁሳቁሶች ወይም መሣሪያዎችን እና መብት የተጣሰባቸው እቃዎችን መያዝ፣ መውረስ እና ማስወገድን ይጨምራል።

👉 ማንም ሰው የሚጠቀምበትን የንግድ ምልክት በሕጉ መሠረት በማስመዝገብ ጥበቃ ማግኘት እንደሚችል በአዋጁ ተደንግጓል። የምርት አከፋፋዮችም የሚሸጡትን ዕቃ ምንነት እና ምንጩን አጣርቶ የንግድ ምልክት ባለቤቱን መብት ማክበር እንደሚጠበቅባቸው አዋጁ ይገልጻል።

ሸማቾችም ትክክለኛውን ምርት በንግድ ምልክታቸው በመለየት ተመሳስለው ከሚሠሩ እና ጥራት የጎደላቸው ምርቶችን ከመጠቀም ራሳቸውን መጠበቅ ይገባቸዋል፡፡

ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ33ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ እንደሚያለማ የሰሜን ጎጃም ዞን ገለጸ።
Next articleየሰላም እጦትን ለመፍታት የጋራ ሥራዎችን በአብሮነት መሥራት ያስፈልጋል።